አጊቱ በጣሊያን ገጠራማ አካባቢ በመኖር ነው ፍየል በማርባት እውቅናን ያገኘችው
በጣሊያን ሀገር የተገደለችው ኢትዮጵያዊት አጊቱ ጉደታ አስከሬን ዛሬ ጠዋት አዲስ አባባ ገብቷል፡፡ አስከሬኑ አዲስ አበባ ሲገባ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይና የሟቿ ቤተሰቦች በሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ተቀብለውታል፡፡
በጣሊያን ሀገር ፍየል በማርባትና የፍየል ተዋጽኦዎችን በማቅረብ የምትታወቀው አጊቱ በሰራተኛዋ መገደሏን ፖሊስ አስታውቆ ነበር፡፡
በፈረንጆቹ 2010 ከኢትዮጵያ በስደት ወደ ጣሊያን በመሔድ በፍየል እርባታና በአትክልት ምርት (በጥምር ግብርና) ውጤታማ በመሆን በተምሳሌትነት የምትጠቀሰው የአጊቱ ሞት፣ በዓለም ሚዲያዎች ተስተጋብቷል፡፡
የዘረኝነት ጥቃት እና ማስፈራሪያ ይደርስባት እንደነበር ከዚህ ቀደም ሪፖርት ከማድረጓ ጋር በተያያዘ ፣ የሞቷ ዜና እንደተሰማ ፣ ምናልባትም የዘረኝነት ሰለባ ሆና ሊሆን እንደሚችል ተገምቶ ነበር፡፡
ይሁንና በእርሻዋ ቀጥራ የምታስሰራው ጋናዊ ሰራተኛዋ የ42 ዓመቷን አጊቱ ጉደታን ስለመግደሉ ዴይሊ ሜይል ዘግቦ ነበር፡፡ የ32 ዓመቱ ጋናዊ አዳምስ ሱሌይማኒ ባልተከፈለ ደመወዝ ዙሪያ በተነሳ አለመግባባት በመዶሻ ገድሏታል ተብሏል፡፡ በመዶሻ መትቷት ወድቃ በጣዕረ ሞት ላይ እያለች እንደደፈራትም የጣሊያን ሚዲያዎች መዘገባቸውን ዴይሊ ሜይል መዘገቡ ይታወሳል፡፡