ኢትዮጵያዊቷ አጊቱ ጉደታ በጋናዊ ሰራተኛዋ መገደሏ ተገለጸ
ከ10 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ በስደት ጣሊያን የገባቸው አጊቱ በተወዳጅ የአይብ ምርቷም ትታወቃለች
በጣሊያን ገጠራማ ስፍራ በግብርና ስራዋ ዝናን ያተረፈችው ኢትዮጵያዊት አጊቱ ጉደታ ትናንት ነበር ሞታ የተገኘችው
በጣሊያን አልፓይን ገጠራማ አካባቢ ተወዳጅ የፍየል አይብ እያዘጋጀች ለገበያ በማቅረብ የምትታወቀው ኢትዮጵያዊት አጊቱ ኢዴዎ ጉደታ በእርሻ ቦታዋ ላይ መገደሏን ትናንት ፖሊስ አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2010 ከኢትዮጵያ በስደት ወደ ጣሊያን በመሔድ በፍየል እርባታና በአትክልት ምርት (በጥምር ግብርና) ውጤታማ በመሆን በተምሳሌትነት የምትጠቀሰው የአጊቱ ሞት፣ በዓለም ሚዲያዎች ተስተጋብቷል፡፡
የዘረኝነት ጥቃት እና ማስፈራሪያ ይደርስባት እንደነበር ከዚህ ቀደም ሪፖርት ከማድረጓ ጋር በተያያዘ ፣ የሞቷ ዜና እንደተሰማ ፣ ምናልባትም የዘረኝነት ሰለባ ሆና ሊሆን እንደሚችል ተገምቶ ነበር፡፡
ይሁንና በእርሻዋ ቀጥራ የምታስሰራው ጋናዊ ሰራተኛዋ የ42 ዓመቷን አጊቱ ጉደታን ስለመግደሉ ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡ የ32 ዓመቱ ጋናዊ አዳምስ ሱሌይማኒ ባልተከፈለ ደመወዝ ዙሪያ በተነሳ አለመግባባት በመዶሻ ገድሏታል ተብሏል፡፡ በመዶሻ መትቷት ወድቃ በጣዕረ ሞት ላይ እያለች እንደደፈራትም የጣሊያን ሚዲያዎች መዘገባቸውን ዴይሊ ሜይል አንስቷል፡፡
ስኬታማዋ የቢስነስ ሴት አጊቱ ፣በቫል ዴ ሞቼኒ መኖሪያ ቤቷን ሰርታ ትኖር የነበረ ሲሆን በጣሊያን ስደተኞች ላይ ጥላቻ እየጨመረ በሄደበት ወቅት አንፀባራቂ ታሪክ ያላት ስደተኛ ተደርጋ ትታይ ነበር፡፡
ከተወዳጁ የፍየል አይብ በተጨማሪ ላ ካፕራ ፌሊስ (La Capra Felice) ወይም the Happy Goat (ደስተኛ ፍየል) የሚል ስያሜ በሰጠችው እና ቀደም ሲል አያስፈልግም ተብሎ በተተወ የእርሻ መሬቷ ላይ በምታመርታው የመዋቢያ ምርቶችም ትታወቃለች፡፡
የእርሻ ቦታውን ስታዘጋች የተቃወማት እንዳልነበረ እና እና በሂደት በስራዋ ታዋቂ መሆኗን በአውሮፓውያኑ 2018 ከሮይተርስ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ገልጻ ነበር፡፡ በዚሁ ዓመት የዘረኝነት ማስፈራሪያ እና ጥቃት ደርሶባት እንደነበረም የገለጸች ሲሆን ፣ በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ አጊቱ ላይ ጉዳት አድርሶ የነበረ አንድ ግለሰብ ለ9 ወራት ታስሯል፡፡ ይሔው ግለሰብ በሞቷም ተጠርጥሮ ምርመራ ቢደረግበትም ከውጀሉ ነጻ መሆኑን የዘገበው ዴይሊ ሜይል፡፡ ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ ሱሌይማኒ የተባለው ተቀጣሪዋ አጂቱን መግደሉን ካመነ በኋላ ሌሊቱን በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልቷል፡፡
በ15 ፍየሎች የእርባታ ስራዋን የጀመረችው አጊቱ በ2018 ዝናዋ በናኘበት ወቅት 180 ፍየሎች ነበሯት፡፡