በአዲስ አበባ በህቡዕ ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ በነበረ ቡድን ላይ እርምጃ መወሰዱን የጸጥታ እና ደህንነት ግብረ ሀይል አስታወቀ
ግብረ ሀይሉ በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ሊፈጸም የነበረን የሽብር ድርጊት ማክሸፉን ገልጿል
ናሁሰናይ አንዳርጌ የተባለ የቡድኑ አመራር እና ሌሎች አባላት በጸጥታ ሀይሎች ተገድለዋል ተብሏል
በአዲስ አበባ በህቡዕ በተደራጀ ቡድን ላይ እርምጃ መውሰዱን የጸጥታ እና ደህንነት ግብረ ሀይል አስታወቀ።
የጸጥታ እና ደህንነት ግብረ ሀይል ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ በህቡዕ የተደራጀ "ጽንፈኛ" ቡድን መኖሩ ተደርሶበታል ሲል ገልጿል።
መንግስታዊ ብዙሀን መገናኛዎች የግብረ ሀይሉን መግለጫ ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ የዚህ ህቡዕ "ጽንፈኛ" ቡድን አመራር እና አባላት ላይ የጸጥታ ሀይሎች እርምጃ ተወስዶባቸዋል።
ናሁሰናይ አንዳርጌ ታረቀኝ በተባለ ግለሰብ የሚመራ ቡድን በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የጥፋት ድርጊቶች ሊፈጽም ሲል ተደርሶበታልም ተብሏል።
የጸጥታ ሀይሎች በወሰዱት እርምጃም ነሁሰናይ አንዳርጌ ታረቀኝ እና አቤነዘር ጋሻው አባተ ከጽጥታ ሀይሎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደላቸውም ተገልጿል።
የህቡዕ ቡድኑ አመራር ነበር የተባለው ናሁሰናይ አንዳርጌ ያሰበውን የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም ወጣቶችን እንደመለመለ፣ ስልጠና ለመስጠት እና ለእቅዱም መሳካት ገንዘብ ከሀገር ውስጥ እና ውጭ ሀገር ከሚገኙ ደጋፊዎቹ ማሰባሰቡም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የጸጥታ ሀይሎችም ይህን ህቡዕ ቡድን ሲከታተሉ እንደነበር የገለጸው መግለጫው በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2C 14373 አአ ተሽከርካሪን በመጠቀም ሲንቀሳቀሱ እጅ እንዲሰጡ ቢጠየቁም ተኩስ ከፍተዋል ተብሏል።
በዚህ የተኩስ ልውውጥም ሁለት የፖሊስ አባላት ሲቆስሉ ባለ ተሽከርካሪው አቶ እንደሻው ጌትነት እንደተገደሉ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የአዲስ አበባ ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ከጸጥታ ሀይሎች ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ያቀረበው የጸጥታ እና ደህንነት ግብረ ሀይሉ እንደ ሆቴል እና እንግዳ ማረፊያ ቤቶች ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳቧል።
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን "መልሼ አደራጃለሁ" የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ በአማራ ክልል ግጭት ተከስቷል።
ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሟል።
የፍትህ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቲየስ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት በአማራ ክልል በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ መናገራቸው ይታወሳል።