ሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራ ዳግም እንደምትጀምር አስታወቀች
ሰሜን ኮሪያ የንዩክሌር እና የአህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ ዳግም እንደምትጀምር የሀገሪቱ መሪ አስታወቁ፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከዩኤስ አሜሪካ ጋር በነበረው ድርድር የተቋረጠው የንዩክሌር እና ረዥም ርቀት ሚሳይል ሙከራ ዳግም እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
ሀገራቸው አዲስ የጦር መሳሪያ በቅርቡ ለዓለም እንደምታስተዋውቅም የገለጹት ኪም፣ ከአሜሪካ ጋር ዳግም ለመደራደር ዝግጁ እንደሆኑ እና ማንኛውም ሙከራ በአሜሪካ አቋም ይወሰናል ብለዋል፡፡
ፒዮንግያንግ የንዩክሌር መርሀ ግብሯን ሙሉ በሙሉ እስካላቆመች ዋሺንግተን በሀገሪቱ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንደማታነሳ ከያዘችው አቋም ፈቀቅ ባለማለቷ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠረ የመጣው ተግባቦት እየተቀዛቀዘ ዳግም ወደ መካረር መጥተዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያ ከባለአንጣዋ ዋሺንግተን ጋር በነበራት ድርድር አሜሪካ ግዛት የሚደርስ አህጉር አቋራች ሚሳይልን ጨምሮ አደርጋለሁ ብላ በእቅዷ ይዛ የነበረውን የተለያዩ የንዩክሌር መሳሪያ ሙከራዎች በጊዜያዊነትም ቢሆን አቋርጣ ቆይታለች፡፡ ከአውሮፓውያኑ 2017 ወዲህ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከባድ የሚባል ሙከራ በፒዮንግያንግ አልተደፈረም፡፡
ይሁንና በ2019 መገባደጃ ወራት፣ የአሜሪካን ግትር አቋም ለማስቀየር ያለመ፣ ተደጋጋሚ የመለስተኛ ሚሳይሎች ሙከራ በሀገሪቱ ተደርጓል፡፡
ኪም ጆንግ ኡን ታዲያ፣ በአውሮፓውያኑ 2020 አዲስ ዓመት የመጀመሪያ እለት፣ ይሄን የማስፈራሪያ መልዕክት ያስተላለፉት፣ ከፓርቲያቸው አመራሮች ጋር ለአራት ቀናት ከመከሩ በኋላ ነው፡፡
አሜሪካ በማዕቀቧ በቀጠለችበትና ከደቡብ ኮሪያ ጋር የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓን ባጠናከረችበት ሁኔታ፣ ከዚህ በኋላ ሰሜን ኮሪያ በገዛ ፈቃዷ ባቆመችው የሚሳይል ሙከራ ለመቀጠል አትገደድም ሲል የሀገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል፡፡
እስካሁን ሀገራቸው ለስምምነቱ ተገዢ ሆና ብትቆይም አሜሪካ ግን ማዕቀቧን በማጠናከር ኢኮኖሚያቸውን ክፉኛ እየጎዳች እንደሆነ ያወሱት ኪም፣ ከዚህ በኋላ ሰሜን ኮሪያውያን ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ችግሮቻችንን በራሳችን አቅም ለመፍታት መጽናት አለብን ሲሉም፣ በአሜሪካ ተስፋ መቁረጣቸውን በሚያሳይ መልኩ፣ ለህዝባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ