በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የላ ሊጋ ውድድርን ጨምሮ በርካታ ስፖርታዊ ክዋኔዎች እንዲቋረጡ ተወስኗል
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የላ ሊጋ ውድድርን ጨምሮ በርካታ ስፖርታዊ ክዋኔዎች እንዲቋረጡ ተወስኗል
የጁቬንቲዩስ ተከላካይ ዳኒኤል ሩጋኒ በቫይረሱ መያዙን ክለቡ አስታውቋል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ ተጫዋቹን ጨምሮ ሌሎች የክለቡ አባላትም እንዲለዩ ተደርጓል፡፡
ተጫዋቹ በትዊተር ገጹ ባስተላለፈው መልእክት “ዜናውን ሰምታችሁ ለምትጨነቁልኝ ሁሉ ደህና መሆኔን አረጋግጣለሁ፤ ቫይረሱ ማንንም የማይለይ በመሆኑ ለራሳችንና ለምንወዳቸው ስንል ማድረግ ያለብንን ጥንቃቄ ሁሉ እናድርግ” ብሏል፡፡
ከቫይረሱ ስጋት ጋር በተያያዘ የጣሊያን ሊግ ቢያንስ እስከመጋቢት 25 እንዲቋረጥ የተወሰነ ከመሆኑም ባለፈ፣ ሊጉ ላይጠናቀቅ እንደሚችልም የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የላ ሊጋ ውድድርም እንዲቋረጥ ተወስኗል፡፡
ተወዳጁ የስፔን ላ ሊጋ እንዲቋረጥ የተወሰነው ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ የሪያል ማድሪድ ተጫዋቾች ለይቶ ማቆያ ማእከል በመግባታቸው ነው፡፡
የልምምድ ቁሳቁሶችን የሚያቀርብ አንድ የክለቡ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች በቫይረሱ መያዙ በመረጋገጡ ክለቡ የእግር ኳስ እንዲሁም የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾቹ በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ወስኗል፡፡
ሁለተኛው ዲቪዚዮንም የተቋረጠ ሲሆን የማድሪድ ተጫዋቾች ለ2 ሳምንታት ተለይተው ከቆዩ በኋላ ላ ሊጋው ውሳኔውን እንደሚገመግም አስታውቋል፡፡
በላ ሊጋ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማድሪድ በነገው እለት በላ ሊጋ ውድድር ኤይባርን፣ በቀጣዩ ማክሰኞ ደግሞ ከማንችስተር ሲቲ ጋር የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታውን ለማድረግ መርሀ-ግብር ተይዞለት ነበር፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት ዓለማቀፍ ወረርሽን ተብሎ የተፈረጀው ኮሮና ቫይረስ በመላው ዓለም በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡
በአሜሪካ ተወዳጅ የሆነው የቅርጫት ኳስ ውድድር ተቋርጦ እንዲቆይ የተወሰነ ሲሆን ዛሬ ይካሄዱ የነበሩ የዩሮፓ ሊግ ሁለት ጨዋታዎችም ተራዝመዋል፡፡ የማንቺስተር ዩናይትድን ጨምሮ በርካታ ጨዋታዎች ግን ብዙዎቹ በዝግ ስታዲዮም ይካሄዳሉ፡፡
እስካሁን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከ118 ሺ በላይ ሰዎች የተጠቁ ሲሆን ከ 4,300 በላይ የሚሆኑት ለሞት ተዳርገዋል፤ የተለያዩ ምንጮች እንደዘገቡት፡፡