ለዚህም በልዩ ህክምና በሰለጠኑ አነፍናፊ ውሾች ላይ ተስፋ ተጥሏል
በልዩ ህክምና የሰለጠኑ ውሾች ኮሮና ቫይረስን በማነፍነፍ መለየት እንዲችሉ እየተሞከረ ነው
በልዩ የህክምና ልየታ የሰለጠኑ ውሾች ሃገራት እየተፈተኑ ላሉበት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ መፍትሄ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተስፋ ተደርጓል፡፡
በአንድ ሰዓት ውስጥ ብቻ 750 ሰዎችን ማነፍነፍ ይችላሉ የተባለላቸው የህክምና ውሾቹ የኮሮና ኬዞችን ለይተው ማወቅ ይችሉ እንደሆነ ለማረጋገጥ በለንደን ጤና እና ትሮፒካል ህክምና ትምህርት ቤት፣በዱርሃም ዩኒቨርስቲ እና የህክምና ውሾችን በሚያሰለጥኑ ተቋማት በኩል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ውሾቹ በተጨባጭ በቫይረሱ የተያዘን ሰው መለየት ይችሉ እንደሁ ለማወቅም ተቋማቱ በቅድሚያ 6 ውሾችን ለማሰልጠን አስበዋል ቢዝነስ ኢንሳይደርን ዋቢ እንዳደረገው የሳይንስ አለርት ዘገባ፡፡
ስልጠናው ውሾቹ ቫይረሱን በጠረን እንዲለዩ (COVID-19 odor detection) ማድረግን ያካትታል፡፡ ለዚህም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሲጠቀሙበት የነበረውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ጭምብል) እንዲያነፈንፉ ይደረጋል፡፡
ይህ ግን ሳምንታትን ምናልባትም ወራትን ሊወስድ የሚችል ነው፡፡
ሃሳቡ የሚሳካ ከሆነ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረትም ሆነ በህክምናው ዘርፍ እንደ ትልቅ እመርታ ሆኖ ይመዘገባል፡፡
በእንዲህ ዓይነት መንገድ የሰለጠኑ ውሾች ከአሁን ቀደምም ካንሰር፣ወባንና ፓርኪንሰንን መሰል በሽታዎች ሲለዩ ነበር፡፡