ሱዳን ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል መዘጋጀቷን አስታወቀች፡፡
ትናንት ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄኔራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር ሳይታሰብ ኡጋንዳ ላይ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ከአልቡርሃን ጋር በነበራቸው ውይይት እስራኤል ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ ብሎም ትልቅ ደረጃ ማድረስ እንደምትፈልግ እስራኤል ትናንት ገልጻለች፡፡
ውይይቱን በመገናኛ ብዙሀን የሰሙት የዓረብ ሀገራት ባለስልጣናት ሱዳንን እንደ ከዳተኛ በማየት ጉዳዩን ከፍተኛ መነጋገሪያ አድርገውታል፡፡ ከዓረብ ሊግ 22 ሀገራት ሱዳንን ጨምሮ 19ኙ እስካሁን እንደ ሀገር ለእስራኤል እውቅና ያልሰጡ መሆናቸው ልብ ይሏል፡፡
ስለውይይቱ እንደ ማንኛውም አካል በመገናኛ ብዙሀን ከመስማታቸው ውጭ ፕሬዚዳንት አልቡርሃን በኡጋንዳ ስለሚያደርጉት ጉብኝትም ሆነ ከእስራኤል ጋር ስለተደረገው ውይይት መረጃ እንደሌላቸው ያስታወቁት የሱዳን መንግስት ቃል አቀባይ ፈይሰል ሳሊህ፣ በጉዳዩ ላይ ፕሬዝዳንቱ ሲመለሱ ማብራሪያ ይሰጣል ብለው ነበር፡፡
በዚህም መሰረት ፕሬዝዳንቱ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ዛሬ በሰጡት መግለጫ የሁለቱ መሪዎች ውይይት ከሁለት ወራት በፊት የታቀደ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ውይይቱም በዋሺንግተን አቀናባሪነት የተዘጋጀ መሆኑን በመጠቆም ሀገራቸው ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ማቀዷን ይፋ አድርገዋል፡፡
ከኔታኒያሁ ጋር ያደረጉት ውይይት የሱዳንን ህዝብ ጥቅም ማዕከል ያደረገ ነው ያሉት አልቡርሃን፤ ይሄንንም በቅርቡ በሚመጣ የኢኮኖሚ ለውጥ እናሳያለን ብለዋል፡፡
በሁለቱ መካከል የጠደረገው ውይይት ለሽግግር መንግስቱ ምክር ቤት ቀርቦ፣ የመጨረሻ የውሳኔ ሀሳቡን ምክር ቤቱ በቅርቡ ለእስራኤል እንደሚያሳውቅም ፕሬዝዳንት አልቡርሃን ተናግረዋል፡፡
ሱዳን በጀርባዬ ወጋችኝ ያለችውን ፍልስጤምንና ሌሎች የእስራኤል ባላኝጣዎችን ይበልጥ በሚያበግን መልኩ፣ ሁሉም የሱዳን ፖለቲከኞች የሚደርስባቸውን ተጽእኖ ፈርተው እንጂ ከእስራኤል ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር ይፈልጋሉ ሲሉም ይፋ አድርገዋል፡፡
የሀገሪቱ ጦር ውይይቱን በማድነቅ ለአልቡርሃን ያለውን ድጋፍ ገልጿል፡፡
በሽግግር ወቅት ላይ የምትገኘው ሱዳን መረጋጋትን ማስፈን ባልቻለችበት በዚህ ጊዜ ከእስራኤል ጋር መሰለፏ አሁንም የዓረቡን አለም ማነጋገሩን ቀጥሏል፡፡