ከምርጫው በኋላ አዲስ ሕገ መንግስት እንደሚጸድቅና አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሾም ይጠበቃል
ሶሪያ የፓርላማ ምርጫ እያደረገች ነው
ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ የእርስ በእርስ ጦርነት መገለጫዋ የሆነው ሶሪያ ፣ ዜጎቿ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ተበትነው ለስቃይ፣ ለልመናና ለሌሎችም ችግሮች ተጋልጠዋል፡፡
በባሽር አል አሳድና በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ጦርነት ደማስቆስን፣አሌፖንና ሌሎች ታሪካዊና ጥንታዊ ከተሞችን ክፉኛ አውድሟል፡፡ የሶሪያ ጉዳይ በዉጭ ሀገራት ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት መታጀቡ ፖለቲካዋን የከፋ አድርጎታል፡፡
ይህ ሁሉ ብጥብጥና ችግር እያለ ታዲያ ሀገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ምርጫ ለማድረግ ማሰቧ ሲገለጽ ቆይቷል፡ ፡በሚያዚያ ወር ሊካሔድ ታስቦ የነበረውና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስተጓጎለው ይህ ምርጫ ዛሬ እየተከናወነ መሆኑ ነው ይፋ የተደረገው፡፡
ምርጫው እየተካሄደ ያለው የሶሪያው ፕሬዚዳንት ባሽር አልአሳድ ስልጣን የያዙበትን 20ኛ ዓመት እያከበሩ ባለበት ጊዜ መሆኑንም ብዙኃን መገኛዎች እየዘገቡ ናቸው፡፡
በሶሪያ አሁንም ጦርነትና የኢኮኖሚ ድቀት ቢኖርም ሀገሪቱ ምርጫ እያረገች መሆኗ ግን አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ለምክር ቤት አባልነት እየተካሄደ ባለው ምርጫ ባለሀብቶች መካተታቸው ተጠቅሷል፡፡ በቅርቡ በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው የግል ባለሀብቶች ለሕግ አውጪው ም/ቤት ምርጫ እየተወዳደሩ መሆናቸውም ይፋ ተደርጓል፡፡
በሚያዚያ ወር ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ምርጫ ነው አሁን እየተካሄደ ያለው፡፡ ከምርጫው በኋላ አዲሱ ምክር ቤት አዲስ ሕገ መንግስት ያጸድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በሽር አል አሳድም አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚመርጡ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የባሽር አል አሳድን መንግስት የሚቃወሙ ሰዎች በምርጫው ዝርዝር ውስጥ አለመኖራቸው የተገለጸ ሲሆን ምርጫው ለይስሙላ የሚከናወን ነው የሚል ስም ተስጥቶታል፡፡
ምርጫው ተአማኒነት የሌለው መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎች እየገለጹ ናቸው፡፡ ለዚህ መነሻ ያደረጉት ደግሞ ተወዳዳሪዎቹ የፕሬዚዳንቱ ደጋዎች አሊያም የፓርቲያቸው ሰዎች ናቸው የሚል ሆኗል፡፡ በርካታ ሶሪያውያን እንደሚሉት ምርጫው ሂደቱና ውጤቱ በገግዥው መንግስት እየተወሰነ ያለ በመሆኑ ትርጉም አልባ ነው፡፡
ዋረዲ ካራም ሻር በመካከለኛው ምስራቅ ተቋም የሶሪያ ጉዳዮች ተንታኝ ሲሆን እርሱ እንደሚለው ፕሬዚዳት አሳድ ይህንን የፓርላማ ምርጫ የሚጠቀሙበት ታማኝነትን ለማግኘት ነው፡፡
በእርስ በርስ ጦርነት እየተናጠች ባለችው ሶሪያ የአሳድ ጦር በአውሮፓውያን 2018 ምስራቃዊ ጎታን እንድሁም በ2019 ደቡባዊ ኢድሊብን መቆጣጠር ችሏል፡፡ ሌሎች የኢድሊብ ክፍሎች ግን በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው እየተገለጸ ያለው፡፡
በዚህ መሃል የሚደረግ ምርጫ አሁን ላይ ለሀገሪቱም ለመንግስትም በስደትና በተገን ፍለጋ ላይ ላሉትም እርባና እንደሌለው ነው የሶሪያ ጉዳዮች ተንታኙ የሚያነሱት፡፡ ምርጫው እየተደረገ ያለው ከ7ሺ በሚበልጡ የምርጫ ጣቢያዎች ሲሆን ይህም የሶሪያን 70 በመቶ ግዛት ያካትታል ነው የተባለው፡፡ የሀገሪቱ መንግስት በአማጺያን ቁጥጥር ስር ያሉ ግዛቶችን ለማስመለስ ጥረት እያደረገ ነውም ተብሏል፡፡