ኑ ወደ ባቢሌ እንሂድ!
“ባቢሌ ምልክቷ ብዙ ነው፤ የደመ ግቡዎች መዲና ናት”
ሄኖክ ስዩም (ተጓዡ ጋዜጠኛ) የዝኆኖች መጠለያ የኾነችውን መስህብ ፍለጋ ተጉዟል
ኑ ወደ ባቢሌ እንሂድ!
ዛሬ ቅዳሜ ነው፤ ቅዳሜ ባቢሌ ደርሶ የሚያውቀው የእኩለ ቀኑ ድባብ ይገዝፍበታል፡፡ ከአዲስ አበባ ጅግጅጋ የሚጓዝ ሀረርን እንዳለፈ ሞቅ ያለች ከተማ ካገኘ እሷ ባቢሌ ናት፡፡
ባቢሌ ምልክቷ ብዙ ነው፤ የደመ ግቡዎች መዲና ናት፡፡ ደማቅ የንግድ እንቅስቃሴ መገለጫዋ ነው፡፡ ጎዳናዋ ግርግር አያጣም፡፡ መንገደኛው መኪና ሁሉ ጨክኖ አያልፋትም፤ መንገድ ሳትሆን ማረፊያ ናት፡፡
የመጣሁት የዝኆኖችን መጠለያ ፍለጋ ነው፡፡ ብዙ ቋንቋ እሰማለሁ፤ ባቢሌ ላይ የባቢሌን ነዋሪ መለየት አይከብድም ባቢሌዎች በቀላሉ ተግባቢ ናቸው፡፡ ጎዳናዋ ላይ ዓይኑን ለወረወረ የጫት ገበያዎችን ይመለከታል፡፡ ግን ብቻቸውን አይደሉም፤ ጥላ የተዘረጋላቸው የለውዝ ትሪዎች፤ አጠገባቸው ደግሞ የፍራፍሬ ድርድር፤ ባቢሌ የንግድ ከተማ ናት፡፡ እንደ ጂኤፍ የገባ የማይወጣባቸው ደግ ቤቶች ብዙ ናቸው፡፡ ኮረብታውን ታኮ የቆመው መስጂድ የከተማዋ የውበት መገለጫ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ከስምንት እስከ አስር አረፍ ትላለች፤ መልሶ መሸት ሲል ግርግሩ ይቀጥላል፡፡
ጥብሳ ጥብሱ ጎዳናዋ ላይ አይጠፋም፡፡ ሰው ባለው የሚቀምስባት ከተማ ናት፡፡ አደምን ብዬ መጥቻለሁ፤ ከቤን ብዬ ደርሻለሁ፡፡ የባቢሌ ዝኆኖችን ፍለጋ፤ ወደ ከተማዋ ዳርቻ ልወጣ ነው፡፡ እነኛ ምትሃተኛ ድንጋዮች ሰው ያፈዛሉ፡፡ የጅግጅጋን መንገድ ይዛችሁ አምስት ኪሎ ሜትር ተጓዙ፤ እዚህ ጋር ነው ባይ አያስፈልግም፤ የዳካታ ድንጋዮች ተንጠራርተው እዚህ ጋር ነን ይላሉ፡፡
አቤት አሰራር! ተፈጥሮ ትችልበታለች፡፡ አንዱ ድንጋይ ሌላ የድንጋይ ቆብ አድርጓል ፤ ተደርድረዋል፤ አንዱ ሌላውን አይመስልም፤ የየራሳቸው ውበት፣ የየራሳቸው አቀማመጥ፣ የየራሳቸው ገጽ አላቸው ፤ የዳካታ ትክል ድንጋዮች፡፡ ጉርሱምም ኮምቦልቻም እንዲህ መሰል ድንጋይ ታዩ ይሆናል፡፡ ይሄኛው ግን ብዙ ነው፤ ዓይነቱም ቁጥሩም፡፡ መኪኖቹ በጎዳናው ይከንፋሉ፤ ገና ወደ ኤረር ሸለቆ እንገባለን፡፡ ቅዳሜን በምናብ እንዲህ ያለ ቦታ ማሳለፍ መታደል ነው፡፡
በፊቅ በኩል ተጓዝን፤ የተነሳነው ከባቢሌ ነው፡፡ የዳካታ ትክል ድንጋዮች ሸኝተውን ወደ ሱማሌ ክልል ኤረር ዞን ገብተናል፡፡ የባቢሌ ዝኆኖች መጠለያ የትናንትና ክብራችንን ያሳየናል፤ የዛሬውን አብረን እናየዋለን፡፡
የአፍሪቃ ዱር እንስሳት ምዕራባውያን ባይደርሱለት፤ እንግሊዛውያን መቀነታቸውን ባይፈቱለት፤ ጀርመናውያን ስልጠና ብለው ባይባትሉ ዛሬ መልኩ እንዲህ አይሆንም፡፡ እኛ ያለ ቅኝ ገዢ ድካም በነጻ ምድራችን ነጻ የዱር ህይወት ጥበቃ ፍልስፍናን እውን አድርገን ነበር፤ የዝኆንን አደን የአጼ ምንልክ ህግ ሲኮንንና ደንብ ሲያወጣ አፍሪቃ ከብዝሃ ህይወት ልማት ጋር አንዳች እውቀት አልነበራትም፡፡
አዲሱ ወደ ፊቅ የሚወስደው መንገድ በጥሩ ሁኔታ እየታነጸ ነው፡፡ እኔ ስለቀደመው የዝኆን ጥበቃ ፍልስፍና መርሃችን እያብሰለሰልኩ ከባዱን ፒስታ መንገድ ጀመርነው፡፡ ጉዞው በቁጥቋጦ ግራና ቀኝ ታጅቦ ወደሚሞቀው ሸለቆ ቀጠለ፡፡
አልፎ አልፎ የሱማሌ አርብቶ አደሮች ጎጆና የሚያማምሩ በግና ፍየሎች ቁጥቋጦውም ወረው ይታያል፡፡ ጠፍ መንደሮች ደጋግመው ከዐይኔ ይገባሉ፡፡ ወደ ባቢሌ ዝኆኖች መጠለያ አንድ ክፍል እየተጓዝን ነው፡፡
የባቢሌ ዝኆኖች መጠለያ በ1962 ዓ.ም. የተመሰረተ ነው፡፡ ጓዱን እየቀበረ፤ በጥይት እየተመታ፤ ከዝኆን መርዶ ያልተላቀቀ፤
ምስራቅ ኢትዮጵያ ጌጧ የባቢሌ ዝኆኖች መጠለያ ነበር፤ በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች የሚገኘው ይህ ብዝሃ ህይወት ሁለት ክልል ያረፈ፤ አመለ ቢሱ ፌዴራሊዝማችን ተደማምጦ ሀብት ለመጠበቅ እንኳን እድል እንደተነፈገው ያሳየ፤ በዝኆን ስም የሚጠራው ባቢሌ ከ31 በላይ የጡት አጥቢ ዱር እንስሳ ዝርያዎች መኖሪያ ነው፡፡ የወፍ ዝርያው ራሱ ከ220 በላይ እንደሚደርስ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ አሁን እየሄድሁ ያለሁት ከባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ አንዱ ወደሆነው ውብ የሁለት ሸለቆዎች ጋብቻ መፈጸሚያ ሥነ ምህዳር ነው፡፡ መልኩ የሚለየውን፣ ግርማው የሚያስፈራውን መከራ የበዛበት ዝኆን ፍለጋ፤ መኪናው ቆመ፤ ከመኪና እንውረድ አሉ፡፡ ሁላችንም ወረንድ፤ ዓይኔም ከመኪና እንደወረደ ቁልቁል ወረደ፡፡ ሸለቆው ተአምራዊ ነበር፡፡ ጎበሌ ከኤረር ጋብቻ ፈጽሞ በኤረር ስም ወደ ዋቢ ሸበሌ መንገድ የሚጀምርበት ስፍራ፡፡
እንዴት እንደሚያምር፤ በዚያ የራሱ ሸለቆ ላይ እየጋለበ ምድሩን ሰንጥቆ ጎበሌ ወንዝ እዚህ ደርሷል፡፡ በዚህ እንደ ጎበሌ ኤረር ግዙፍ ሸለቆ ፈጥሮ መጥቷል፡፡ ሁለቱ የሚገናኙበት ስፍራ አናት ቆሜያለሁ፡፡ የወንዙ ዳርቻ ውብ ነው፡፡ በግራና በቀኝ የመመልከቻ ማማዎቹ ለቅንጡ ሪዞርቶች ምቹ ናቸው፡፡ ከመመለሴ በፊት ጎበሌ ከኤረር ተዋህዶ ወደ ዋቢሸበሌ ሲሄድ በዓይኖቼ ሸኘሁት፡፡…
ይህ የቅኝት መጣጥፍ የተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ሲሆን በድሬ ቲዩብ ላይ የቀረበ ነው፡፡