የኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት ምንድ ነው
ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባው ወደ ውጪ ከምትልከው በ6 እጥፍ ይበልጣል
ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባው ወደ ውጪ ከምትልከው በ6 እጥፍ ይበልጣል
የኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት (Macro-Economic Imbalance ) ምንድ ነው?
ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሚዲያዎች፤ በመንግስት ባለስልጣናት እና በኢኮኖሚስቶች አንደበት በተደጋጋሚ ስለሚነገረው እና ሀገራችን ስለገጠማት የኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት ወይም Macro-Economic Imbalance ምንንነት ሃሳቤን በአጭሩ ልግለጽላችሁ!
ኢኮኖሚክስ የሁለት ዘርፍ ውጤት ነው። አንደኛው በቤተሰብ እና በግለሰብ ደረጃ ያለውን የሰዎች ፍላጎት በአላቂው ሃብት ማሟላት ላይ ያተኮረው የMicro-economy ሃሳብ ሲሆን፤ ሁለተኛው የጠቅላላ ሀገራዊ ሁኔታዎችን ስለሚዳስሰው የMacro-economy ሃሳብ ነው፡፡
በ Micro-economy: በቤተሰብ እና በግለሰብ ደረጃ ስለሚኖረው ስለ ዋጋ፤ ስለ አቅርቦት፤ ስለ ፍላጎት፤ ስለ የሰዎች ምርጫ፤ ስለ የሸማች እና አምራቾች ውሳኔ አሰጣጥ፤ ስለ እርካታ፤ ስለ ትርፍ፤ ስለ ወጪ፤ ወዘተ የመጨነቅ እና የማጥናት ጉዳይ ነው፡፡
በ Macro-economy:- ጠቅላላ ሀገራዊ ድምር ሀኔታዎችን ማጥናት ሲሆን፤ ማለትም ስለ የዋጋ ንረት፤ ስለ ስራ አጥነት፤ ስለ የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት እና ስርጭት፤ ስለ ብሄራዊ የእዳ ጫና፤ ስለ ወለድ መጠን፤ ወዘተ የመጨነቅ እና የማጥናት ጉዳይ ነው፡፡
#ለምሳሌ፡- የአንድ ሀገር ጠቅላላ የስራ አጥነት ደረጃ በአማካኝ እስከ ከ4 በመቶ እና ከዛ በታች ሲሆን ጤናማ ይባላል (ኢትዮጲያ ውስጥ በከተማ ብቻ ያለው ስራ አጥነት 30ከመቶ ደርሷል)፤ ጠቅላላ የዋጋ ንረት መጠን ከ5 ከመቶ እና በታች ሲሆን ጤናማ ይባላል (በኢትዮጲያ በጥቅምት ወር ላይ የዋጋ ንረት በ23 ከመቶ አድጎ ወደ 30 ከመቶ መድረሱን አይተናል)፤ የውጪ ምንዛሬ ክምችት ለዓመታት የሚያዛልቅ ሲሆን ጤናማ ይባላል (በኢትዮጲያ ከ3 ወር በላይ የሚያቆይ የውጪ ምንዛሬ ክምችት የለም)፤ ሀገራዊ የእዳ ጫና ዝቅተኛ ሲሆን ጤናማ ይባላል (የኢትዮጲያ የእዳ ጫና ከሀገራዊ ጠቅላላ ምርት አንጻር 49 ከመቶ ደርሷል)፤ የንግድ ሚዛን መመጣጠን ቢቻል አልያም ሀገራት ወደ ውጪ የሚልኩት ወደ ሀገር ውስጥ ከሚያስገቡት መብልጥ ሲችል ጤናማ ይባላል (ኢትዮጲያ ከውጪ የምታስገባው ወደ ውጪ ከምትልከው አንጻር 6 እጥፍ ይበልጣል)፤……….
የኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት ወይም Macro-Economic Imbalance የሚፈጠረው ከላይ ከተዘረዘሩት ዝቅተኛ መነሻ ኢኮኖሚያዊ ደረጃዎች በእጅጉ ርቆ መገኘት ማለት እና ሁኔታዎችን ለማረጋጋት የሚወሰዱ እርምጃዎች ሌሎች ተጨማሪ ሀገራዊ ጉዳቶችን ሲያባብሱ ማለት ነው፡፡ #ለምሳሌ፡- በፖሊሲ አለመጣጣም ምክንያት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የተወሰደ መፍትሄ ስራ አጥነትን ሲያባብስ እንደማለት ነው፡፡
#ለምሳሌ፦ የሀገራችን ጠቅላላ ኢኮኖሚያዊ እድገት (GDP) በሁለት አሀዝ ያድግ በነበረ ወቅት እድገቱ በመንግስት ጠቅላላ ከፍተኛ ወጪ ላይ የተመሰረተ እና መሰረተ ልማት ግንባታን መነሻ ያደረገ ስለነበር ኢኮኖሚው ማደጉን ብቻ በማየታችን የኢኮኖሚው እድገት የዜጎችን ፍላጎት አሳድጎት የዋጋ ንረትን ሲያቀጣጥለው እንደነበር መገንዘብ አልተቻለም ነበር።
በእርግጥ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት የአጭር ግዜ እና የአንድ ምክንያት ውጤት አይደለም! ስለዚህ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለተከታታይ ዓመታት በፖሊሲ እና በመፈፀም አቅም ላይ ተመርኩዞ ጠንካራ ስራዎችን በመስራት የሚቃና ጉዳይ መሆኑ መታወቅ አለበት።
ማስታወሻ፡ በዚህ መጣጥፍ የተካተቱ ይዘቶች ጸሃፊውን እንጂ አል ዐይን አማርኛን የሚመለከቱ አልያም የአል ዐይንን አቋም የሚያንጸባርቁ አይደሉም