በቦክሲንግ ዴይ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች አፍሪካውያን ኮኮቦች ነግሰው አምሽተዋል
በቦክሲንግ ዴይ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች አፍሪካውያን ኮኮቦች ነግሰው አምሽተዋል
ትናንት ምሽት በተጀመሩ የገና ሰሞን የቦክሲንግ ዴይ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች አፍሪካውያኑ የኳስ ክዋክብት ደምቀውና ነግሰው አምሽተዋል፡፡
ቶትንሃም ብራይተንን 2 ለ1 ባሸነፈበት ጨዋታ ኮትዲቯራዊው ተከላካይ ሰርጊ አውሬር ለእንግሊዙ አማካይ ዴሊ አሊ ያሻገራት ኳስ በመመራት ላይ የነበረውን ቶትንሃምን ለአሸናፊነት ከማብቃት ባሻገር በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 5ኛነትን እንዲቀዳጅ አድርጋለች፡፡
ጋቦናዊው የአርሰናል የፊት መስመር ተጫዋች ፔሬ ኤምሬክ አቦሚያንግም ከቦርንማውዝ ጋር 1 ለ 1 በተለያዩበት ጨዋታ የአቻነቷን ጎል አስቆጥሯል፡፡ይህም ለአዲሱ አሰልጣኝ ለሚኬል አርቴታ ጅማሮ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡
ጋናዊው የፊት መስመር ተጫዋች ጆርዳን አዪው ያስቆጠራት ጎል ዌስትሃምን በሴልኸርስት ፓርክ ያስተናገደው ክሪስታል ፓላስ 1 ለ 0 ከመመራት ተነስቶ 2 ለ 1 እንዲያሸንፍ አስችላለች፡፡ አዪው በጭንቅላቱ ወደ ኋላ የገጫትን ኳስ ወደ ጎል ከቀየረው ሴኒጋላዊው ቼኩ ኩዬቴ የአቻነት ጎል በኋላ አዪው 4 የዌስትሃም ተጫዋቾችን አጣጥፎ በማለፍ ነበረ በግሩም ሁኔታ የማሸነፊያዋን ጎል ያስቆጠረው፡፡
ቼልሲ ያልተጠበቀ የ2 ለ 0 ሽንፈትን ባስተናገደበት የስታምፎርድ ብሪጅ ጨዋታ ናይጄሪያዊ ዝርያ ያለው ሚካዔል ኦባፌሚ ለሳውዝሃምፕተን ጎል አስቆጥሯል፡፡ የ19 ዓመቱ አየር ላንዳዊው ኢንተርናሽናል ኦባፌሚ በ19 ዓመት ከ173 ቀናት ዕድሜው በስታምፎርድ ብሪጅ የፕሪሚዬር ሊግ ጎል ያስቆጠረ ቀዳሚው ተጫዋች ሆኗል፡፡ ይህም 2007 ወርሃ ግንቦት ላይ በ18 ዓመት ከ303 ቀኑ በብሪጅ ጎል ካስቆጠረው የኤቨርተኑ ተጫዋች ጄምስ ቫጋን በኋላ የመጀመሪያው ያደርገዋል፡፡
የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ እግር ኳስ ተጫዋቾች ዝርዝርን የሚመሩት ሞሃመድ ሳላህና ሳዲዮ ማኔም እንደተለመደው ሁሉ በትናንት ምሽት የቦክሲንግ ዴይ ጨዋታዎች ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ ሊቨርፑል ሌስተርን 4 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ ናይጄሪያዊው ኬሌቺ ኢሃይናቾም ተሰልፎ ነበር፡፡ የአምናው ሻምፒዮን ማንችስተር ሲቲ ዎልቭስን በሚገጥምበት ጨዋታ አልጄሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ የተሸለ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግም ይጠበቃል፡፡