ከ70 ኪሎሜትሮች በላይ ያለ ሾፌር የተጓዘው የህንድ ባቡር
ሾፌርና ረዳቱ በተረኛ ለመተካት እንደወረዱ በራሱ መጓዝ የጀመረው ባቡር አምስት የባቡር ጣቢያዎችን ካለፈ በኋላ እንዲቆም ተደርጓል
በስአት 100 ኪሎሜትር የተምዘገዘገው ባቡር በሰዎች ላይ ጉዳት አላደረሰም ተብሏል
በህንድ ያለምንም ሾፌር ከ70 ኪሎሜትሮች በላይ የተጓዘው እቃ ጫኝ ባቡር መነጋገሪያ ሆኗል።
ባቡሩ በከፍተኛ ፍጥነት በርካታ የባቡር ጣቢያዎችን እያቆራረጠ ሲያልፍ የሚያሳዩ ምስሎችም በማህበራዊ ሚዲያዎች ተለቀዋል።
እቃ ጫኝ ባቡሩ ከጃሙ እና ካሽሚር ወደ ፑንጃቧ ሆሺያፑር በመጓዝ ላይ ነበር ተብሏል።
የባቡሩ አሽከርካሪና ረዳቱ ካቱዋ በተባለችው ከተማ ለተረኛ አሽከርካሪዎች ለማስረከብ እንደወረዱ ቆሞ የነበረው ባቡር በራሱ ጉዞ መጀመሩን የህንዱ ፕረስ ትረስት የዜና ወኪል ዘግቧል።
ባቡሩ ቆሞበት የነበረው ስፍራ ተዳፋታማ መሆኑ ጉዞውን እንዲቀጥል ሳያደርገው እንደማይቀርም በማከል።
53 ተጎታች ወይም ዋገን ያለው ባቡር ለግንባታ የሚውል አሽዋና ድንጋይ ጭኖ ነበር የተባለ ሲሆን፥ አምስት የባቡር ጣቢያዎችን ካቋረጠ በኋላ እንዲቆም ተደርጓል።
ያለ ሾፌርና ረዳት ከ70 ኪሎሜትሮች በላይ የተጓዘው ባቡር የተጓዘበት ፍጥነትም በስአት 100 ኪሎሜትር ገደማ እንደነበር ነው የተገለጸው።
በፍጥነት ሲጓዝ የነበረውን ባቡር ለማስቆም በሃዲዱ ላይ የእንጨት ርብራብ መደረጉን ነው የህንድ ሬልወይስ ያስታወቀው።
የክስተቱ ዋነኛ መንስኤ እንዲጣራ ያዘዘው ተቋሙ ያለሾፌር የተጓዘው ባቡር ምንም አይነት ጉዳት አላደረሰም ብሏል።
መቆም ባልፈለገው ባቡር መንገደኞች አደጋ እንዳይደርስባቸውም ሁሉም የባቡር ማቋረጫዎች ዝግ ሆነው መቆየታቸው ተገልጿል።