በህንድ የባቡር ግጭት 300 የሚጠጉ ሰዎች ህይወት አለፈ
የባቡር አደጋው በሀገሪቱ በ20 ዓመታት ከታዩ አደጋዎች በእጅጉ የከፋ ነው ተብሏል
የህንድ ባቡር ሚንስቴር በአደጋው ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል
በህንድ የባቡር ግጭት 300 የሚጠጉ ሰዎች ህይወት አለፈ።
በህንድ ኦዲሻ ግዛት በሁለት የመንገደኞች ባቡሮች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሟች ቁጥር ወደ 288 ከፍ ብሏል።
ከ850 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የመንግስት ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የባቡር አደጋው በሀገሪቱ ከ20 ዓመታት በላይ የተመዘገበ በእጅጉ የከፋ ነው ተብሏል።
የኦዲሻ የእሳት አደጋ አገልግሎት “የህይወት አድን ስራው አሁንም እንደቀጠለ ነው። ብዙ ከባድ ጉዳቶች ደርሰዋል” ብሏል።
አርብ በደረሰው አደጋ ከ200 በላይ አምቡላንሶች ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን ከ180 በላይ ዶክተሮችም ለእርዳታ መሰማራታቸው ተነግሯል።
ከአደጋው የተረፈ አንድ መንገደኛ "ባቡሩ ከሀዲዱ ሲወጣ በጩኸቱ ከእንቅልፌ ነቃሁ። በድንገት ከ10 እስከ15 ሰዎች ሞተው አየሁ። ከባቡሩ መውጣት ችያለሁ፤ ከዚያም ብዙ አስከሬኖች አየሁ" በማለት ስለ አደጋው ተናግሯል።
ግጭቱ የተከሰተው አርብ እለት ከባንጋሎር ወደ ሃዋራ ዌስት ቤንጋል የሚሄደው የሃውራ ፈጣን ኤክስፕረስ እና ከኮልካታ ወደ ቼናይ ከሚሄደው ኮሮማንደል ኤክስፕረስ ጋር በመጋጨታቸው ነው።
ባለሥልጣናቱ በመጀመሪያ የትኛው ባቡር መንገድ ስቶ ተጋጨ ለሚለው የተምታታ ሀሳብ ማቅረባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሀገሪቱ የባቡር ሚንስቴር በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
ምንም እንኳን አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች በአደጋው ላይ የጭነት ባቡር ጭምር መሳተፉን ቢጠቁሙም፤ በባለስልጣናቱ በኩል ስለ ጉዳዩ ላይ የተባለ ነገር የለም።