በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ላይ ያተኮረው ሁለተኛ ዙር የሶስትዮሽ ውይይት በግብጽ መካሄድ ጀመረ፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ጉዳይ ላይ የሚመክረው ሁለተኛ ዙር የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች የቴክኒክ ስብሰባ ዛሬ በካይሮ መካሄድ እንደጀመረ ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ስብሰባው ህዳር 5 እና 6 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው ስብሰባ ውይይት ተደርጎባቸው የጋራ መግባባት ባልተደረሰባቸው የህዳሴው ግድብ የውሀ ሙሌት እና አለቃቀቅ ዙሪያ ለሁለት ቀናት ምክክር የሚደረግበት ነው፡፡
በግድቡ የውሀ ሙሌት እና ቀጣይ ተግባራት ዙሪያ ሶስቱ ሀገራት የየራሳቸውን አዲስ ሀሳብ በውይይት መድረኩ ይዘው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ግብጽ የኢትዮጵያው ግድብ ከሁለቱ ተደራዳሪ ሀገራት ግድቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ ወደስራ እንዲገባ የሚጡቁም ምክረ ሀሳብ እንደምታቀርብም ይጠበቃል፡፡
በስብሰባው ላይ ንግግር ያደረጉት የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች የግድቡ ሙሌት እና የውኃ አለቃቀቅ በአዲስ አበባ በተጀመረው ውይይት መሰረት እንደሚቀጥልና መግባባት ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
በስብሰባው የዓለም ባንክ እና የአሜሪካ መንግስት ተወካዮች በታዛቢነት እየተሳተፉ እንደሚገኙም ዘገባው አትቷል፡፡
የካይሮው ውይይት በግድቡ የውሀ ሙሌትና አለቃቀቅ ዙሪያ ከሚደረጉ አራት ውይይቶች አንዱ ሲሆን ሶስተኛው ዙር ውይይት ከቀናት በኋላ በሱዳን ካርቱም ተካሂዶ አራተኛውና የማሳረጊያው ውይይት ደግሞ በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ የሚደረግ ይሆናል፡፡