ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለመካከለኛው ምስራቅ አዲስ የሰላም እቅድ አዘጋጅቻለሁ አሉ፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚኒ ኔታኒያ በሚቀጥለው ሳምንት በዋሸንግተን ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ፡፡ በሃገራቸው ፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ ያሉት ኔታንያሁ ወደ ሁነኛ ወዳጃቸው ጋር እንደሚሄዱ ተረጋግጧል፡፡
እርሳቸው በሙስናና በምርጫ ውዝግብ ውስጥ ቢገቡም ለረጅም ጊዜ እስራኤል ትፈልገው የነበረውን የኢየሩሳሌምን መዲናነት አሜሪካ ዕውቅና ሰጥታላታለች፡፡
ቢቢ ወደ አሜሪካ የሚያቀኑት ብቻቸውን እንዳልሆነ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ናቸው፡፡ ይልቁንም ከቀድሞው የእስራኤል የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና ከምርጫ ተቀናቃኛቸው ቤኒ ጋንትዝን ጋር እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
ከሁለቱ የእስራኤል ፖለቲከኞች ጉብኝት አስቀድሞ ታዲያ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ዕቅድን ቀጣይ ማክሰኞ ይፋ እንደያሚደርጉ አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የምርጫ ተቀናቃኛቸው ቤኒ ጋንትዝን በነጩ ቤተ መንግስት ከማነጋገራቸው ቀደም ብለው ነው ዕቅዱን ይፋ እንደሚያደርጉ ሲኤንኤን ያስነበበው፡፡
በሚቀርበው የሰላም እቅድ ላይ ፍልስጥኤማውያን አሉታዊ ምልከታ ሊኖራቸው ይችላል ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ይሁንና የሰላም ዕቅዱ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
ይፋ ይደረጋል የተባለው የሰላም ዕቅድ ለረጅም ጊዜ መፍትሄ ያላገኘውን የእስራኤል ፍልስጥኤም ውዝግብ ይፈታል ብለዋል፡፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁና የተቀናቃኛቸው ቤኒ ጋንትዝ ጉብኝት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ ከሚደረገው የእስራኤል ምርጫ አስቀድሞ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ፕሬዝዳት ትራምፕ የእስራኤልን ፖለቲከኞች በነጩ ቤተ መንግስ የሚጋብዙት አሁን ያለባቸውን ክስ አቅጣጫ ለማስቀየርና ለማረሳሳት ነው የሚሉም አሉ፡፡
ይፋ ሊደረግ የታሰበው የሰላም ዕቅድም ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የሚገመት ሲሆን እርሳቸውን በቀጣናው ውሳኔ እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡
ቤኒያሚን ኔታንያሁና የብሉ ኤንድ ኋይት አሊያንስ ፓርቲ ሊቀመንበር ቤኒ ጋንትዝ ከትራምፕ ጋር በመካከለኛው ምስራቅና የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ በኢሩሳሌም የሰነበቱት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ አስታውቀዋል፡፡
አዲሱ የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ዕቅድ በዋናነት የተመራውና የተዘጋጀው በትራምፕ አማችና ከፍተኛ አማካሪ ጃሬድ ኩሽነር አማካኝነት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ዕቅዱ እስካሁን የዘገየው በእስራኤል ፖለቲካ መረጋጋት ስላልነበር ነው ተብሏል፡፡
የሰላም ዕቅዱ የእስራኤል ፍልስጥኤምን ጉዳይ እንደሚመለከት ፍንጭ ቢሰጥም የሶሪያን፣ የየመንን፣ የገልፍ ሃገራትን ችግሮችና ሌሎች በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ዓለም አንገብጋቢ የሚላቸውን ጉዳዮች በተመለከተ የተባለ ነገር የለም፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን