“ወቅቱ አንድነት የሚጎለብትበት እንጂ የገንዘብ ድጋፍ የሚቋረጥበት አይደለም”
ትራምፕ ሃገራቸው ለዓለም ጤና ድርጅት የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጧን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ውሳኔ ኮንነዋል
“ወቅቱ አንድነት የሚጎለብትበት እንጂ የገንዘብ ድጋፍ የሚቋረጥበት አይደለም”
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃገራቸው ለዓለም ጤና ድርጅት የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጧን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ምላሾች እየተሰጡ ነው፡፡
ትራምፕ አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል ለሆነው የዓለም ጤና ድርጅት የምትሰጠውን ገንዘብ ልታቋርጥ መሆኑን ማስታወቃቸውን ተከትሎ ጊዜው አሁን አይደለም የሚሉ አስተያየቶችም እየተሰሙ ይገኛል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “አሁን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት የሚደረግበት፣አንድነት የሚጎለብትበት እንጂ የገንዘብ ድጋፍ የሚቋረጥበት አይደለም” ሲሉ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የዓለም ጤና ድርጅት “የኮሮና ቫይረሰ ስርጭትን ሸፋፍኗል፤ በአግባቡም አልመራም” በሚል ተቋሙን ተጠያቂ ካደረጉት ሰነባብተዋል፡፡
በቅርቡ ድርጅቱ “ለቻይና እያዳላ ነው (China centric) ስለሆነም አሜሪካ የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ታቆማለች” የሚል ሃሳብ መሰንዘራቸውም ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሰረት ነው ወደ ጄኔቭ ይላክ የነበረውን ገንዘብ ማስቆማቸው የተሰማው፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በአውሮፓውያኑ 2020 እንደ አባል አገር ከፍተኛ ገንዘብ የሚያዋጡት አገራትና የገንዘብ መጠኑ
አሜሪካ 57 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር፣
ቻይና 28 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር፣
ጃፓን 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር፣
ጀርመን 14 ነጥብ 6 ፣
ብሪታኒያ 10 ነጥብ 9
ፈረንሳይ 10 ነጥብ 6
ጣሊያን 7 ነጥብ 9
ብራዚል 7 ነጥብ 1 ናቸው፡፡
ይሁንና ይህ መዋጮ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት አባልነት ብቻ የሚከፈል ሲሆን በፈቃደኝነት መለገስም ይቻላል፡፡ ለአብነትም አሜሪካ እ.ኤ.አ በ2019 400 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ልገሳን ለድርጅቱ ማበርከቷን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ትራምፕ “ከወደ ቻይና የሚገኙ መረጃዎችን ብቻ በመከተል እንድንዘናጋ፤ከወደ ቻይና የሚመጡ ዜጎች ወደ ሃገራችን እንዳይገቡ ለማድረግ የጣልነው እገዳ እንዳይሳካ አድርጎናል፤ከህይወትም በላይ ፖለቲካን አስቀድሟል” በሚል ለሚኮንኑት ተቋም አሜሪካ እ.ኤ.አ በ2018 እና 2019 በድምሩ 893 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ ስለማድረጓም ዴይሊ ሜይል አስነብቧል፡፡