በፍጥነት በመዛመት ላይ የሚገኘውን ኮሮና ቫይረስ ራስን ባለማጋለጥ መከላከል የተሻለው አማራጭ ነው፡፡
በፍጥነት በመዛመት ላይ የሚገኘውን ኮሮና ቫይረስ ራስን ባለማጋለጥ መከላከል የተሻለው አማራጭ ነው፡፡
ባለፈው ታህሳስ ወር መነሻውን በቻይናዋ ዉሀን ከተማ ያደረገው ኮሮና ቫይረስ አሁን ከቻይና ውጭም የደቀነው ስጋት አይሏል፡፡
ቫይረሱ እስካሁን ባጠቃላይ ከ82 ሺ በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ፣ ከ2,800 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለህልፈት ዳርጓል፡፡ የቫይረሱ ስርጭትም ከአንታርክቲካ ውጭ ሁሉንም አህጉራት አዳርሷል፡፡
ምንም እንኳን ከ78,600 በላይ ዜጎቿ ተጠቅተውባት እስካሁን 2,747 ዜጎቿን ያጣችው ቻይና የቫይረሱ ዋነኛ ተጠቂ ብትሆንም፣ አሁን ቫይረሱ ከቻይና ውጭም በፍጥነት እየተዛመተ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ ከቻይና የበለጠ የተጠቂዎች ሪፖርት ከሌሎች ሀገራት እንደደረሰው ትናንት የካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም መግለጹ ይታወሳል፡፡
ከቻይና ውጭ በድምሩ ከ 3,000 በላይ ተጠቂዎች ሲኖሩ ከ 50 በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ኢራን ጭምብል ያደረጉ ዜጎች
ከቻይና ቀጥላ ዋነኛ ተጠቂ የሆነችው ደግሞ ደቡብ ኮሪያ ናት፡፡ በሀገሪቱ እስከዛሬ ባለው ሪፖርት መሰረት 1,766 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 13 ሞት ተመዝግቧል፡፡
ከዳያመንድ ፕሪንሰስ ክሩይዝ መርከብ ጋር በተያያዘ ጃፓንም በርካታ የቫይረሱ ታማሚዎች የሚገኙባት ሀገር ናት፡፡ በሀገሪቱ ከሚገኙ 800 ያህል የቫይረሱ ተጠቂዎች መካከል ከ700 በላይ የሚሆኑት 3,700 ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ በነበረው መርከብ ላይ የተያዙ ናቸው፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ 141 ተጠቂዎች ያሉባትና 22 ሰዎች የሞቱባት ኢራን ደግሞ ትከተላለች፡፡
አውሮፓዊቷ ሀገር ጣሊያን ደግሞ 400 ተጠቂዎች ያሉባት ሲሆን 12 ሰዎችን በቫይረሱ አጥታለች፡፡
ቫይረሱ ቀድሞ ከተዳረሰባቸው ሀገራት በተጨማሪ ባለፉት 7 ቀናት ብቻ የኮሮና ቫይረስ ሃያ አዳዲስ ሀገራት ደርሷል፡፡
በሳምንቱ ቫይረሱ ከተዳረሰባቸው አዳዲስ ሀገራት መካከል አብዛኛው የመካከለኛው ምስራቅና የአውሮፓ ሀገራት ናቸው፡፡ በዋናነት የተዛመተው ደግሞ ከኢራን እና ጣሊያን ነው፡፡
በጣሊያን ጭምብል አድርጎ በምቀሳቀስ ተለምዷል
አዳዲስ ተጠቂዎች ሊባኖስ፣ ኦማን፣ እስራኤል፣ አፍጋኒስታን፣ ግሪክ፣ ዴንማሪክ፣ ኦስትራ፣ ኢስቶኒያ፣ ሮማኒያ፣ ሰሜን መቄዶንያ፣ ጆርጂያ፣ ፓኪስታን፣ ኖርዌይ፣ ስፔን፣ ብራዚል፣ አልጄሪያ፣ ስዊዘሪላንድ፣ ክሮሽያ፣ ባህሬን እና ኵዌት ናቸው፡፡
ለመሆኑ አሳሳቢው ኮሮና ቫይረስ ምንድነው?
ኮሮና ቫይረስ የቫይረሶች ቤተሰብ ነው፡፡ ከእንስሳት ወደ ሰው፣ ከሰው ወደ ሰውም ይተላለፋል፡፡
በቫይረሱ የተያዘ ሰው ከፍተኛ ትኩሳት፣ሳል እና ለመተንፈስ የመቸገር ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ቫይረሱ የሚያስከትለው ህመም ከጉንፋን ጀምሮ የመተንፈሻ አካላትን በከፍተኛ ደረጃ ያጠቃል፡፡
ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ፡- የሳምባ ምች፣የመተንፈሻ አካላት ከባድ ህመም፣ የኩላሊት ስራ ማቆም እና ሞት ያስከትላል፡፡ ቫይረሱ ክትባትም መድኃኒትም አልተገኘለትም፡፡
ራስን ከኮሮና ቫይረስ እንዴት መከላከል ይቻላል?
ለቫይረሱ ራስን አለማጋለጥ የተሻለው የመከላከያ አማራጭ ነው፡፡
የቅድመ መከላከያ መንገዶች፡-
• እጅን ቶሎ ቶሎ በሳሙና መታጠብ
• ዐይን አፍንጫና አፍን በእጅ አለመነካካት
• በሚያስነጥሱበት ጊዜ አፍና አፍንጫን በሶፍትአሊያም በእጅዎ ክንድ መሸፈን
• የተጠቀሙትን ሶፍት በአግባቡ ማስወገድ
• ምልክቱ ከታየበት ሰው ጋር የቀረበ ግንኙነት አለማድረግ
• ጭምብል መጠቀም ከፈለጉ አፍና አፍንጫዎን በአግባቡ መሸፈን
• ጭምብሉን ካደረጉ በኋላ በእጅዎ አይነካኩት
• የተጠቀሙት ጭምብል በጥንቃቄ ማስወገድ
• የእንስሳት ተዋጽኦዎችን አብስሎ መመገብ
• ምልክት ከታየብዎት ወዲያውኑ ወደጤና ተቋም መሄድ
ሀገራት ቫይረሱን ለመከላከል ሲባል የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድም ጀምረዋል፡፡ የቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኢራን እና ጣሊያን አጎራባች ሀገራት በአብዛኛው ድንበሮቻቸውን መዝጋት እና ዜጎቻቸው ወደነዚህ ሀገራት በሚያደርጓቸው ጉዞዎች ላይ እገዳ ማስቀመጥ ጀምረዋል፡፡
የተለያዩ ምንጮችን ለዜናው በዋቢነት ተጠቅመናል፡፡