መንግስት አካሄድኩ ካለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ማግስት ምጣኔ ሃብቱ ምን ይምሰል?
ተቋማትን ዳግም ማደራጀትም ለኢኮኖሚ መነቃቃት ሌላው መሰረታዊ እርምጃ ነው
“ተፈናቃዮችን ከመመለስ እና መሰረተ ልማትን መልሶ ከመገንባት ባለፈ ምጣኔ ሃብቱን ማነቃቃት ያስፈልጋል”- ዋሲሁን በላይ (ኢኮኖሚስት)
መንግስት አካሄድኩ ካለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ማግስት ምጣኔ ሃብቱ ምን ይምሰል?
በከፍተኛ ሁኔታ ቋሚ ንብረቶች የወደሙበት፤ ብዙዎች የሞቱበት፤ ብዙዎች የቆሰሉበት እና ብዙዎች የተሰደዱበት ጦርነት መጠናቀቁን ተከትሎ በሂደቱ የወደመውን ኢኮኖሚያዊ እና ሰብዓዊ ክስረት ለማሻሻል እና በቀጣይ ከቀውስ ማግስት (Economy after War) ኢኮኖሚው ምን መምሰል እንዳለበት ሃሳቦቻችንን ብንለዋወጥ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በመጀመሪያ በአማራ በተለይ ከትግራይ ጋር በሚዋሰኑበት አካባቢ እንዲሁም በትግራይ ክልል ለሚኖሩ ንፁሃን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ የሚቀርብበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል፡፡
ለዚህ ደግሞ መንግስት የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ለጋሽ ሀገራትን፣ግለሰቦችን እና ድርጅቶችን በማስተባበር ድጋፍ እንዲቀርብ ማድረግ መጀመር አለበት።
የጦርነት አካባቢዎች ከአደጋ የፀዱ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ስራ በመስራት የተሰደዱ ዜጎችን በቂ ማጣራት በማድረግ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በማድረግ መደበኛ ህይወት እንዲጀመር ማድረግም ተገቢ ነው፡፡
ምክንያቱም ማረስ (የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል መሰብሰብ ርብርብ ይፈልጋል)፣ ማምረት፣ መሸጥ፣ መግዛት፣ መማር፣ ወ.ዘ.ተ በመጀመር በቀጠናው ኢኮኖሚው መነቃቃት መጀመር ይኖርበታል።
ተቋማትን በድጋሚ ማቋቋም
ለኢኮኖሚ መነቃቃት ሌላው መሰረታዊ እርምጃ ተቋማትን ድጋሚ ማቋቋም መጀመር ነው፡፡
ስለዚህ ጠንካራ ተቋማት ለልማት በሚቆረቆሩ ሰዎች እንዲመሰረት ማድረግ ገበያው ነፍስ መዝራት እንዲጀምር ማድረግ ይችላል።
የተዘረፉ የፋይናንስ ተቋማት (ባንኮች) ሀብት እንዲመለስ የማጥራት ስራ በመስራት፤ የተዘጉ አካውንቶች የሚፈለገውን ምርመራ በፍጥነት በማጠናቀቅ እና ጤናማውን ወደ ስርዓት በመመለስ ኢኮኖሚው ድጋሚ መነሳት እንዲጀምር ማድረግ ይገባል (ባንኮች ተዘግተው የሚቆዩበት ግዜን ማሳጠር)።
ቢያንስ ባለፉት 25 ቀናት ተቋማት መሰረታቸውን ስተው እንደነበር መገመት ቀላል ነው።
ሀገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ ለተቀረው ዓለም በአግባቡ የማስረዳት የህዝብ ግንኙነት ስራ በመስራት የሰብዓዊ ድጋፍ እና የመሰረተ ልማት መልሶ ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን መንግስት የተለያዩ የግል ድርጅቶች በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶች የሚገነቡበት ሁኔታ ላይ ያቅማቸውን እገዛ እንዲያደርጉ የማስተባበር ስራ ሊሰራ ይገባል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን መደገፍ ካለባቸው ወቅት መካከል አሁን ያለንበት ግዜ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም ከውጪ ምንዛሬ እስከ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ሁኔታዎች ቶሎ መሻሻል እንዲያሳይ ማገዝ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
ጦርነቱ ከዚህ ቀደም በውድ የውጪ ምንዛሬ የተገዙ የሚሊተሪ ግብዓቶችን ( የጦር መሳሪያ፣ የነዳጅ ሪዘርቭ እና መሰል ሃብቶች) ያወደመ በመሆኑ በፍጥነት የመተካት ስራ በመስራት ወደ ፊት ሊፈጠር የሚችልን አደጋ መጋፈጥ በሚችል መልኩ ማደራጀት አስፈላጊ ነው። ጠንካራ ሚሊተሪ የጠንካራ ኢኮኖሚ አቻ ነው፡፡
መንግስት ተጨማሪ በጀት፤ የውጪ እርዳታ እና ብድር በማመቻቸት መሰረተ ልማትን መልሶ ማቋቋም እና የትኩረት አቅጣጫዎች ወደ ልማት በፍጥነት ማዞር እንዲሁም የፓርቲ እና የመንግስት የልማት ተቋማትን የማጥራት ስራ ቢሰራም ይበጃል።
የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የማነቃቂያ ፓኬጅ ማዘጋጀት ( መሬት፣ ብድር፣ የታክስ እፎይታ፣ ጥበቃ፣ ወዘተ) የሀብት ባለቤትነትን የማጣራት ስራ መስራት፣ የልማት ተቋማትን ወደ ግል የማዞሩን ስራ ማፋጠን (ቴሌ፣ ስኳር ፋብሪካ፣ ወዘተ)፣ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተሳታፊነት ማሳደግ፣ የተቋማትን አቅም መፈተሽ፣ በዜጎች መካከል ጤናማ የግንኙነት መስመር የሚዘረጉ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት ወዘተ በቀጣይ ኢኮኖሚያችን በፍጥነት በአጭር ግዜ ውስጥ ከገጠመው ክስተት ለማገገም እድል ይፈጥርለታል ብዬ አስባለሁ።
ማስታወሻ፡ በዚህ መጣጥፍ የተካተቱ ይዘቶች ጸሃፊውን እንጂ አል ዐይን አማርኛን የሚመለከቱ አለበለዚያም የአል ዐይንን አቋም የሚያንጸባርቁ አይደሉም