ጽንፈኛ ታጣቂዎች በ100 ሞተር ሳይክሎች 2 መንደሮች ውስጥ ገብተው ነው ጥቃቱን የፈጸሙት
አሸባሪ ታጣቂዎች ቅዳሜ ዕለት በሁለት የኒጀር መንደሮች በፈጸሙት ጥቃት የተገደሉ ንጹሃን ሰዎች ቁጥር 100 መድረሱን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የመጀመሪያ ዙር ውጤት እንደተገለጸ ፣ በቾማ ባንጉ እና በዛሮማዳሬዬ መንደሮች ላይ ፣ 100 ሞተር ሳይክል እየነዱ በመጡ አሸባሪዎች ነው ጥቃጡ የተፈጸመው፡፡
መንደሮቹ የሚገኙበት የቶነዲኪዊነዲ አካባቢ አስተዳዳሪ አልሙ ሀሰን እንደገለጹት ፣ በጥቃቱ በቾማ ባንጉ መንደር 70 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በዛሮማዳሬዬ ደግሞ 30 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ሁለቱ መንደሮች ከዋና ከተማው ኒያሚ በስተሰሜን 120 ኪ.ሜ (75 ማይል) ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
ሀሰን እንዳሉት “በተጨማሪም 75 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን ፣ የተወሰኑት ወደ ኒያሚ እና ወደ ኦዋላም ተወስደዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈጸሙት በ7 ኪሎ ሜትር ተራርቀው ወደ ሚገኙት ወደ ሁለቱ መንደሮች ተከፋፍለው በመግባት ነው፡፡
የኒጀር ጠቅላይ ሚኒስትር ብሪጊ ራፊኒ እሁድ ዕለት ልዑካንን አስከትለው ጥቃቱ የተፈጸመበትን ስፍራ የጎበኙ ሲሆን ፕሬዝዳንት መሃማዱ ኢሱፉ ደግሞ ዛሬ ከጸጥታው ምክር ቤት ጋር ልዩ ስብሰባ ያደርጋሉ፡፡
የኒጀር የምርጫ ባለስልጣናት በሀገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የመጀመሪያ ውጤት የገዢው ፓርቲ እጩ እና የቀድሞው ሚኒስትር ሞሀመድ ባዙም ማሸነፋቸውን ባስታወቁበት ቅዳሜ ዕለት ፣ ወዲያውኑ እኩለ ቀን ላይ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው፡፡ ባዙም በጂሃዲስቶች ላይ የሚደረገውን ዘመቻ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ባለፈው ዓመትም በኒጀር ታጣቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት ዳርገዋል፡፡