በሁለት መንደሮች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ነው ንጹሃን ሰዎች የተገደሉት
ኒጀር ከማሊ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ ፣ በሁለት መንደሮች ላይ በአንድ ጊዜ በተፈፀሙ ጥቃቶች ቢያንስ 70 ሲቪሎች መገደላቸውን የደህንነት ምንጮች ትናንት ቅዳሜ ገልፀዋል፡፡
ጥቃቱን ኒጀር የሚገኙ እስላማዊ አክራሪ ታጣቂዎች እንደፈጸሙት ተገምቷል፡፡ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው በቾምባንጎ መንደር ወደ 49 የሚጠጉ የመንደሩ ነዋሪዎች የተገደሉ ሲሆን 17 ሰዎች መቁሰላቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የደህንነት ምንጭ ተናግረዋል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሁለተኛው የመረጃ ምንጭ ፣ የኒጀር የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን ደግሞ በዛሩምዳሬዬ መንደር ሌሎች ወደ 30 የሚጠጉ የመንደሩ ነዋሪዎች ተገድለዋል ብለዋል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ፣ ከአልቃይዳ እና ከእስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) ጋር ግንኙነት ባላቸው እስላማዊ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደምም ተደጋጋሚ ጥቃቶች ደርሶባታል። ሀገሪቱ በ ምዕራባዊ ድንበር ከማሊ እና ቡርኪናፋሶ ጋር እንዲሁም በደቡብ ምስራቅ ከናይጄሪያ ጋር በምትዋሰንባቸው ድንበሮች አቅራቢያ በተፈጸሙ ጥቃቶች ባለፈው ዓመት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተገድለውባታል፡፡