ይህ ጥቃት በ2022፣ 100 ሰዎች እንዲገደሉ እና ሌሎች 300 እንዲቆስሉ ምክንያት ከሆኑት ሁለት ፍንዳታዎች ወዲህ በሀገሪቱ ትልቅ የሚባል ነው ተብሏል
በሶማሊያ ባህር ዳርቻ በተፈጸመ ጥቃት 32 ሰዎች ተገደሉ።
በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሹ በሚገኘው ተወዳጅ የባህር ዳርቻ መዝናኛ ቦታ አርብ ምሽት በተፈጸመ ጥቃት 32 ሰዎች ሲገደሉ 63 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የሀገሪቱ ፖሊስ ገልጿል።
ጥቃቱን እስላማዊው ታጣቂ አል ሸባብ እንደፈጸመው የሶማሊያ ሚዲያዎች መጥቀሳቸውን ሮይርስ ዘግቧል።
ይህ ጥቃች በፈረንጆቹ 2022 በገበያ አደራሽ ቅራቢያ በመኪና ላይ ተጠምደው 100 ሰዎች እንዲገደሉ እና ሌሎች 300 ሰዎች እንዲቆስሉ ምክንያት ከሆኑት ሁለት ፍንዳታዎች ወዲህ በሀገሪቱ ትልቅ የሚባል ነው ተብሏል።
ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አልሸባብ ከስአታት በፊት ለጥቃቱ ኃላፊነቱን መውሰዱን አሶሼትድ ፕረስ አስነብቧል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት አብዲላቲፍ ኤደን አርብ እለት በተፈጸመው ጥቃት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ይፋ አድርገዋል።
ኤደን እንደገለጹት ከንጹሃን በተጨማሪ ከጥቃት አድራሾቹ አንዱ ራሱን ሲያጠፋ ሌሎች ሶስቱ ደግሞ በጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል። ከጥቃት አድራሾቹ አንዱ በህይወት ሲያዝ፣ አንድ ፖሊስም በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ተገድሏል።
የሶማሊያ መንግስት ሚዲያ የሆነው ሶና አምስት የአል ሸባብ ታጣቂዎች መገደላቸውን እና ስድስተኛው ራሱን ማጥፋቱን ቀደም ብለው ዘግበዋል።
በኤክስ የተለቀቀ ቪዲዮ የሰዎች አስከሬን በመዝናኛ ቦታው ወድቀው እና ሌሎች ደግሞ ራሳቸውን ለማዳን ሲሮጡ ያሳያል።
አል ሸባብ መንግስት ከ2022 ደምሮ ባደረገው መልሶ ማጥቃት ከማፈግፈጉ በፊት፣ በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ ታጣቃዎቹ አሁን በመንግስት፣ በንግድ እና በወታደራዊ ተቋማት ላይ ጉልህ የሚባል ጥቃት እያደረሱ ናቸው።