የቱርክ ፓርላማ የሀገሪቱ ጦር በሶማሊያ እንዲሰማራ ፈቀደ
ፓርላማው በፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን የቀረበውን የቱርክ ጦርን ለሁለት አመት ወደ ሶማሊያ የማሰማራት እቅድ አጽድቆታል
አንካራ በውጭ ሀገር ግዙፍ የጦር ሰፈር የገነባችው በሶማሊያ ነው
የቱርክ ፓርላማ የሀገሪቱ ጦር በሶማሊያ እንዲሰማራ ፈቀደ።
ፓርላማው ሽብርን ለመዋጋትና ሌሎች ስጋቶችን ለመከላከል የቱርክ ባህር ሃይል ወደ ሶማሊያ ይሰማራ ዘንድ በፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን የቀረበውን የድጋፍ ጥያቄ (ሞሽን) ተቀብሎ አጽድቆታል።
በዚህም መሰረት የቱርክ ባህር ሃይል በቅርቡ ወደ ሞቃዲሾ እንደሚያመራ ነው ቲአርቲ ወርልድ ያስነበበው።
በፕሬዝዳንት ኤርዶሃን የተፈረመው ሞሽን ቱርክ ባለፉት 10 አመታት የሶማሊያ ጦር አቅሙን እንዲያደረጅና ሽብርተኝነት፣ የባህር ላይ ዝርፊያና ሌሎች ወንጀሎችን ለመመከት እንዲችል ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን አመላክቷል።
ቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በፈረንጆቹ 2011 በሞቃዲሾ ጉብኝት ካደረጉ ከስድስት አመታት በኋላ ከግዛቷ ውጭ ትልቅ የተባለውን ወታደራዊ ሰፈር በሞቃዲሾ ገንብታለች።
አንካራ ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ በኤደን ባህረ ሰላጤ በታጠቁ ሃይሎች የሚፈጸሙ ዝርፊያዎችን ለመከላከል ከሌሎች ሀገራት ጋር በትብብር ስትሰራ መቆየቷም ይነገራል።
ሁለቱ ሀገራት በቅርቡም የ10 አመት ወታደራዊ ትብብር ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፥ የባህር ሃይሏን ወደ ሞቃዲሾ የምትልከው አንካራ በሶማሊያ የባህር ጠረፍ የነዳጅ እና ጋዝ ፍለጋ ለማካሄድ ተስማምታለች።
ኢትዮጵያ ሶማሊያ የግዛቷ አንድ አካል አድርጋ ከምታያት ሶማሊላንድ ጋር ባለፈው ታህሳስ ወር የወደብ ስምምነት ስትፈራረም የሞቃዲሾ የግዛት አንድነት ይከበር ካሉ ሀገራት መካከል ቱርክ አንዷ ናት።
አንካራ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ባለፈው ወር ጠርታ ድርድር እንዲጀምሩ ያደረገች ሲሆን፥ ንግግሩ ተስፋ ሰጪ መሆኑን መግለጿም ይታወሳል።
በመስከረም ወርም ሁለተኛ ዙር ድርድር ይካሄዳል ያለችው ቱርክ በአንካራ በሚካሄደው ድርድር የአመቻቺነት ሚና ብቻ ይኖረኛል ማለቷም አይዘነጋም።