በሶማሊያ የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜን ሲከታተሉ በነበሩ ሰዎች ላይ የቦምብ ጥቃት ተፈጸመ
በመዲናዋ ሞቃዲሾ በተሽከርካሪ ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ የ5 ሰዎች ህይወት ማለፉና ከ20 በላይ መቁሰላቸው ተገልጿል
የሶማሊያ ፖሊስ ለቦምብ ጥቃቱ አልሸባብን ተጠያቂ አድርጓል
በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ።
ጥቃቱ በአንድ ታዋቂ ካፍቴሪያ ውስጥ በስፔን እና እንግሊዝ መካከል የሚካሄደውን የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ለመመልከት በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል።
የሶማሊያ ፖሊስ እንዳስታወቀው በተሽከርካሪ ላይ የተጠመደው ቦምብ ፈንድቶ ካፍቴሪያውን በእሳት አያይዞታል።
“እስካሁን አምስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉና 20 ሰዎች መቁሰላቸውን አረጋግጠናል” ያሉት የፖሊስ ቃል አቀባይ ሜጀር አብዲፊታህ አደን ሃሰን፥ ጥቃቱን የአልሸባብ ታጣቂዎች ፈጽመውታል ብለዋል።
የእሳት አደጋ ሰራተኞች በሶማሊያ ፕሬዝዳንት ቤተመንግስት አቅራቢያ ወደሚገኘው ካፍቴሪያ በፍጥነት በመድረስ ጥፋቱን ለመቀነስ መረባረባቸውን የሶማሊያ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
የሶማሊያ መንግስትን በመቃወም ከ17 አመት በላይ ጥቃቶችን ሲፈጽም የቆየው አልሸባብ እስካሁን ለሞቃዲሾው ጥቃት ሃላፊነቱን አልወሰደም።
ከትናንት በስቲያ ከሞቃዲሾ እስር ቤት ለማምለጥ የሞከሩ አምስት የአልሸባብ ታጣቂዎች መገደላቸው መገለጹ ይታወሳል።
በተኩስ ልውውጡ ሶስት የማረሚያ ቤት ጠባቂዎች መገደላቸውና ከ18 በላይ ታራሚዎች መቁሰላቸውንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ ዳግም ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አልሸባብ ላይ “ሁሉን አቀፍ” ጦርነት ማወጃቸው ይታወሳል።
በዚህም አልሸባብን ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ በርካታ አካባቢዎች ማስለቀቅ መቻሉ ቢነገርም ቡድኑ ባለፈው አመት በመሀል የሀገሪቱ ክፍል አዳዲስ ስፍራዎችን መቆጣጠሩን መግለጹ አይዘነጋም።
አልሸባብ ምንም እንኳን በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪዎች በፈረንጆቹ 2011 ከመዲናዋ ሞቃዲሾ እንዲወጣ ቢደረግም በበርካታ የሶማሊያ ገጠራማ ስፍራዎች አሁንም ድረስ ተጽዕኖው የጎላ ነው ተብሏል።
ቡድኑ በሶማሊያ የፖለቲካ፣ የደህንነት እና የሲቪል ተቋማት ላይ ኢላማ ያደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችንም እየፈጸመ ይገኛል።
ሞቃዲሾ ባለፈው ወርም በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ጦር ከሀገሪቱ የሚወጣበትን ጊዜ እንዲያራዝም መጠየቋ የሚታወስ ነው።