በናይጄሪያ ከአንድ ት/ቤት ባለፈው ሳምንት ታግተው የነበሩት 344 ተማሪዎች ተለቀቁ
በእገታ ላይ በነበሩ ተማሪዎች አማካኝነት ትምሕርት ቤቶች እንዲዘጉ መልዕክት ተላልፎ ነበር
ተማሪዎቹን ያገተው ቦኮ ሀራም እንደሆነ ቢታመንም አጋቾቹ ግን ሌሎች ታጣቂዎች ናቸው ተብሏል
በናይጄሪያ ካጺና ግዛት በሚገኘው ካንካራ ትምህርት ቤት ከሳምንት በፊት በተፈጸመ ጥቃት ከ300 በላይ ወንድ ተማሪዎች ታግተው መወሰዳቸው ተገልጾ ነበር፡፡
የናይጄሪያ ጦር ታዲያ በትናንትናው ዕለት ከሰዓት ላይ 344 ተማሪዎችን ከአጋቾቻቸው ማስለቀቁን የካጺና ግዛት ቃል አቀባይ አብዱ ላባራን ገልጸዋል፡፡ የተለቀቁት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን የተወሰኑ ተማሪዎች አሁንም በእገታ ላይ እንደሚገኙ አንዳንድ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡
በትምሕርት ቤቱ ላይ ጥቃት ፈጽሞ ተማሪዎቹን ያገተው ኢስላማዊው ታጣቂ ቦኮ ሀራም እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ጽንፈኛው ቡድን የተወሰኑ ታጋቾችን በቪዲዮ አሳይቶ እንደነበረም ተጠቁሟል፡፡
ይሁንና ጥቃቱ የተፈጸመበት የካጺና ግዛት ቃል አቀባይ አጋቹ ቦኮ ሀራም አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይልቁንም ራሳቸውን እንደ ኢስላማዊ ታጣቂ የሚቆጥሩ ሌሎች ባንዳዎች ጥቃቱን መፈጸማቸውን ነው ቃል አቀባዩ አብዱ ላባራን ያብራሩት፡፡
ትናንት ሐሙስ ጠዋት ላይ የቦኮ ሃራም ምልክት (ሎጎ) አርፎበት በተለቀቀ ቪዲዮ ከታገቱ ተማሪዎች አንዱ "የምዕራባውያንን ትምህርት የሚያስተምሩ ት/ቤቶች እንዲዘጉ" ለናይጄሪያ መንግስት መልዕክት አስተላልፎ ነበር፡፡
በቪዲዮው ላይ የድካም ስሜት የሚታይባቸው በዛፍ ጥላ ስር የተቀመጡ ተማሪዎች ታይተዋል፡፡ ዘገባው የሲኤንኤን ነው፡፡