በናይጄሪያ ከታገቱት ተማሪዎች መካከል እስካሁን 333 የደረሱበት አልታወቀም
ታጣቂዎቹ በድንገተኛ የተኩስ እሩምታ ያናወጡት ትምህርት ቤቱ 839 ተማሪዎችን ያስተምር ነበረ ተብሏል
200 ገደማው ከእገታ ነጻ ወጥተዋል ተብሏል
በሰሜን ምዕራባዊ ናይጄሪያ ካስቲና ግዛት በታጣቂዎች ከታገቱት ተማሪዎች መካከል 333ቱ እስካሁን የደረሱበት አልታወቁም ተባለ፡፡
ባሳለፍነው አርብ በግዛቱ የሚገኘውን የካንካራ የመንግስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በድንገተኛ የተኩስ እሩምታ ያናወጡት ታጣቂዎቹ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ በርካታ ተማሪዎችን አግተው ወስደዋል ተብሏል፡፡
እንደ ፕሪሚዬር ታይምስ ዘገባ ከሆነ ትምህርት ቤቱ ከጥቃቱ በፊት 839 ተማሪዎችን ያስተምር ነበረ፡፡
ሆኖም ከጥቃቱ በኋላ 333ቱ ተማሪዎች የደረሱበት አልታወቀም፡፡
በታጣቂዎቹ ታግተው እንደሁ ለማስለቀቅም እየተፈለጉ ነው ስለ ሁኔታው ወደ ስፍራው አቅንተው ለነበሩ ከፍተኛ የሃገሪቱ ባለስልጣናት እንዳስረዱት እንደ ግዛቱ ዋና አስተዳዳሪ ገለጻ፡፡
በመፈለግ ላይ ያሉት ተማሪዎች ቁጥር 400 ገደማ ነው ያለው ራሽያን ታይምስ ደግሞ ከታገቱት መካከል 200ው ነጻ ወጥተዋል ሲል ዘግቧል፡፡
ድርጊቱ ፕሬዝዳንት መሃመዱ ቡሃሪን ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከቷል፡፡ መንግስታቸው ተማሪዎቹን እንዲመልስ የሚያሳስቡ ከፍተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችም በመደረግ ላይ ናቸው፡፡
በርካቶችም የሃገሪቱ የደህንነት ተቋማት እንዲፈተሹ ጠይቀዋል፡፡
ድርጊቱን ያወገዙት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም ታጋቾቹ ተማሪዎች በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ አሳስበዋል፡፡
የተማሪዎቹን ደህንነት ለመጠበቅ እና ለማስለቀቅ መንግስታቸው እንደሚሰራ ቃል የገቡት ቡሃሪ የሃገሪቱ ወታደሮች በዘመቻ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ከቦኮ ሃራም ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ተጠርጥሯል፡፡
ቦኮሃራም እ.ኤ.አ በ2014 የቺቦክ ልጃገረዶችን አግቶ መውሰዱ የሚታወስ ነው፡፡