
በኮሮና ቫይረስ ለተጠረጠሩ 4 ኢትዮጵያውያን በቦሌ ክትትል እየተደረገላቸው ነው፡፡
እስካሁን በአጠቃላይ ከቻይና የመጡ 4 ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በለይቶ ማከሚያ ማዕከል ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ፡፡
የቫይረሱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ ሁለቱ የሳል እና የሙቀት ምልክት ያሳዩ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን አልፎ አልፎ ከሚስተዋልባቸው ሳል ውጭ ሌላ ምልክት የለባቸውም ይላል መግለጫው፡፡
ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ደግሞ ምንም ምልክት ባይኖርባቸውም ምልክቱ ከታየበት አንድ ተጠርጣሪ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ክትትል እንዲደረግላቸው ሆኗል፡፡
ከአራቱ ኢትዮጵያውያን ተጠርጣሪዎች የተወሰደው የላብራቶሪ ናሙና ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በሃገር ውስጥ በተደረገላቸው ምርመራ ከ5 የቫይረሱ ዓይነቶች ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል ያለው ሚኒስቴሩ የተጠርጣሪዎቹ ናሙና ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኳል ብሏል፡፡
በተለይም ከቻይና ለመጡ 280 መንገደኞች ለ14 ቀናት የሚቀጥል ክትትል ባረፉበት ቦታ ጭምር እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጿል፡፡
በቦሌ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ ጊዜያዊ የለይቶ መከታተያ ማዕከል መቋቋሙም በመግለጫው ወቅት ተነግሯል፡፡
ማዕከሉ የኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዎችን በጊዜያዊነት ለመከታተል የሚያስችል ሲሆን አስፈላጊው የቁሳቁስና የሰው ኃይል ዝግጅት መደረጉንም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ ዛሬ እንደሰጠው መግለጫ ከሆነ ማዕከሉ 30 ተጠርጣሪዎችን ለመከታተል ያስችላል፡፡
በኮሮና ሊጠቁ የሚችሉ ጽኑ ታማሚዎች የሚታከሙበት ክፍል በቅዱስ ጳውሎስ የተለየ ክፍል ተዘጋጅቷል
በጽኑ ለታመሙና ከፍተኛ የህክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የተለየ ክፍል መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የሚመራ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ የወረርሽኝ ቅድመ ዝግጅት ብሄራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የመጀመሪያ ውይይቱን አድርጓልም ተብሏል፡፡
ግብረ ኃይሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ ሌሎች አግባብነት ያላቸውን አካላት ማካተቱም የተነገረ ሲሆን በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲትዩት የሚመራ የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞም ስራ ስለመጀመሩም ይፋ ሆኗል፡፡
የክልልና የከተማ ጤና ቢሮዎችም አስፈላጊዉን ዝግጅት እንዲያደርጉ መልዕክት የተላለፈ ሲሆን፣ በመግለጫው እንደተጠቆመው፣ ለባለሙያዎችና ለሚመለከታቸው አካላት ስለ ቫይረሱ ስልጠና መስጠት ተጀምሯል፡፡
በቦሌ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ ከቻይና እና አጎራባች ሀገራት ለሚመጡ መንገደኞች የሙቀት ልየታ (thermal screening) እየተደረገ ሲሆን፣ እስከ ጥር 18 ቀን 2012ዓ.ም 20,802 መንገደኞች ልየታ ተደርጓዋል፡፡