በሙምባይ 53 የሚዲያ ባለሙያዎች በኮሮና ተይዘዋል
በቤታቸው ተለይተው እንዲቆዩና እንዲጠነቀቁ የተነገራቸው ሲሆን ከአሁን ቀደም ተገናኝተዋቸው የነበሩ ሰዎችን የመለየት ስራ ይሰራል ተብሏል
ባለሙያዎቹ ወረርሽኙን የተመለከቱ ዘገባዎችን ለመስራት በተንቀሳቀሱበት ወቅት በቫይረሱ ሳይያዙ እንዳልቀረ ተጠርጥሯል
በሙምባይ 53 የሚዲያ ባለሙያዎች በኮሮና ተይዘዋል
በህንድ ሙምባይ የሚሰሩ 53 ሪፖርተሮች፣የካሜራ ባለሙያዎች እና ፎቶግራፈሮች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡን ፍሪ ፕረስ የተሰኘ መጽሄት ዘገበ፡፡
ጋዜጠኞቹ መያዛቸው የተረጋገጠው ከ4 ቀናት በፊት ማለትም ያሳለፍነው ሃሙስና አርብ (ሚያዚያ 8 እና 9) ለ167 የሚዲያ ባለሙያዎች በተደረገው ልዩ ምርመራ ነው፡፡
ምርመራው በአጠቃላይ ለ171 የሚዲያ ባለሙያዎች ነው የተደረገው፡፡ ነገር ግን የ4ቱ ውጤት ገና በመጠበቅ ላይ ነው፡፡
ባለሙያዎቹ በቫይረሱ መያዛቸው ቢረጋገጥም ምልክቶችን በወጉ እያሳዩ አይደለም እንደ ልዩ የምርመራ ጣቢያው ምክትል ጤና መኮንን ዶ/ር ዳክሻ ሻህ ገለጻ፡፡ ለክፉ ሊሰጣቸው በሚችል ደረጃም ላይ አይደሉም፡፡
“በቤታቸው ተለይተው እንዲቆዩና እንዲጠነቀቁ አሳስበናቸዋል” ያሉት ጤና መኮንኑ በቅርቡ ወደ ህክምና ማዕከላት ገብተው አስፈላጊው ሁሉ ክትትል እንደሚደረግላቸውና ከእነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ሰዎች የመለየት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ባለሙያዎቹ ቫይረሱን የተመለከቱ ዘገባዎችን ለመስራት ሲንቀሳቀሱ ለቫይረሱ ሳይጋለጡ እንዳልቀረም ተነግሯል፡፡ ይህ ምናልባትም ከማን ሊይዛቸው እንደቻለና ከማን እንደተገናኙ ለመለየት የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ሊያደርገው እንደሚችል ጤና መኮንኑ ገልጸዋል፡፡
በቫይረሱ ተይዘው ነገር ግን ምልክቶቹን በወጉ ሳያሳዩ የሚቆዩ ተጠቂዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ግን የቫይረሱን የስርጭት መጠን ከፍ ሊያደርግ የሚችል ነው፡፡ ከ4 የቫይረሱ ተጠቂዎች አንዱ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊገጥመው እንደሚችልም ሳይንስ አለርት ዘግቧል፡፡
በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል 25 በመቶ ያህሉ ምንም ዓይነት ምልክቶችን የማያሳዩ ናቸው ያሉት የበሽታዎች ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል (CDC) ዳይሬክተር ሮበርት ሬድፊልድ ቁጥሩ ቀላል በማይባል ደረጃ ቫይረሱን ወደ ሌሎች እንደሚያስተላልፉ ተናግረዋል፡፡
ቫይረሱ ስለመያዛቸው እንኳን በማያውቁ ሰዎች እንደሚተላለፍ የታወቀው ባሳለፍነው ወርሃ የካቲት ላይ ነው፡፡
በወቅቱ በቫይረሱ መያዟን እንኳን ያላወቀች እና አንዲትንም ቀን ታምማ የማታውቅ አንዲት የ20 ዓመት የውሃን ከተማ ነዋሪ ቻይናዊ ወጣት ለ5 የቤተሰብ አባላቷ ቫይረሱን አስተላልፋ እንደነበር ስለመረጋገጡ ‘ጃማ ኔትወርክ’ የተሰኘው የህክምና መጽሄት ዘግቦ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡