በግጭት ምክንያት ፈተናው የሚያልፋቸው ተማሪዎች ክልሎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት በልዩነት እንደሚፈተኑ አገልግሎቱ ገለጸ
ኮምፒውተር እና ሌሎች ግብአቶች ባልተሟሉባቸው አካባቢ ያሉ ተማሪዎች በወረቀት ይፈተናል ብሏል አገልግሎቱ
በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና 701ሺ 200 ተማሪዎች እንደሚቀመጡ የምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ገልጿል
ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በዘንድሮው አመት በኦንላይ አማካኝነት ለሚፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የመፈተኛ ፕላትፎርም ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ፈተናውን በኦንላይን ለመስጠት የሚፈልጉ የግልም እና የመንግስት ትምህርት ቤቶች "ዴስክቶፕ ወይም ላፕቶፕ ኮሚፒዩተሮች፣ የውስጥ ኔትዎርክ፣ የኢንተርኔት መስመር ከበቂ ባንድዊድዝ እና ኮምፒውተር ብዛት ጋር እና የባክ አፕ ፓወር ወይም ጀኔሬተር" ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።
የትምህርት ምዘናና እና ፈናዎች አገልግሎት በኦንላይ ለመፈተን ኮምፒውተር እና ሌሎች ግብአቶች ባልተሟሉበት አካባቢ ያሉ ተማራዎች ደግሞ በወረቀት መፈተን ይችላሉ ብሏል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች ለፈተና የሚሆኑ ግብአቶችን እንዲያሟሉ አይጠየቁም።
በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና 701 ሺ 200 ተማሪዎች እንደሚቀመጡ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ፈተናው በሁለት አይነት መንገድ ይሰጣል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በቂ የኮምፒውተር አቅርቦት ባለባቸው ትምህርት ቤቶች በኦንላይን ተማሪዎች ከቤታቸው ወደ ተመደቡበት ተምህርት ቤት በመሄድ ፈተናውን የሚወስዱ ሲሆን የኮምፒውተር እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች ደግሞ ተማሪዎች ከሰኔ 30 ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች በመግባት ፈተናውን በወረቀት ይፈተናሉ ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት ተማሪዎች ወይም የተማሪ ወላጆች ኮምፒውተሮችን ለማሟላት የሚገደዱበት ምንም አይነት አሰራር የለም ነው ያሉት፡፡
ነገር ግን የኮምፒውተር እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች በግል ኮምፒውተር የመፈትን አቅም እና ፍላጎት ያለው ተማሪ ካለ ከፈተናው 10 ቀናት በፊት የግል ኮምፒውተሩን ለሚመለከተው አካል አስረክቦ አስፈላጊው የቴክኒክ ምርመራ እና ፍተሻ ከተደረገለት በኋላ ፈተናውን መውሰድ ይችላል ብለዋል ዳይሬክተሩ።
በአጠቃላይ በዘንድሮው ፈተና በኦንላይን እና በወረቀት የሚፈተነው ተማሪ ቁጥር ስንት ነው ሲል የጠየቀው አል ዐይን፤ በመላ ሀገሪቱ የኮምፒውተር እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ማሟላት ስራዎች ባለመጠናቀቃቸው በቁጥር አልተለየም የሚል ምላሽ አግኝቷል፡፡
በግጭት አካባቢ የሚገኙ ተማሪዎች ጉዳይ
በሀገሪቱ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች ጉዳይ እንዴት ይታያል የሚለው በብዙሀኑ ሲነሳ የነበረ ጥያቄ ነው፡፡
ከግጭት የተመለሱ እና አሁንም ግጭቶች ባሉባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ከትምህርታቸው የተስተጓጎሉ ተፈታኞች ጉዳይን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ‘’እኛ የምንፈትነው የክልል ትምህርት ቢሮዎች ለፈተና ብቁ ናቸው ብሎ ያስተላለፉልንን ተማሪዎች ነው” ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ይህን ያህል ቁጥር ተማሪ ከፈተናው ውጭ ይሆናል የሚል መረጃ ከክልሎች አልቀረበለንም ብሏል አገልግሎቱ፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጥቅምት 2013 ዓ.ም በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መከከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች ተማራዎች ከትምህርት እና ከፈተና ተስተጓጉለዋል።
ባለፈው አመት ህዳር በፕሬቶሪያ በመንግሰት እና በህወሓት መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በትግራይ የነበሩ ተማራዎች እንዲፈኑ ተደርጓል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ ከአምሰት ወር በኋላ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት ባለመቆሙ፣ በግጭት ቀጣና ያሉ ተማራዎች አሉ።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከፈተና ውጭ የሚሆኑ ተማሪዎች ቁጥር እና ቀጣይ እጣፈንታቸው ምን ይመስላል በሚል በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
የፈተናዎች አገልግሎት በበኩሉ የብሄራዊ ፈተና ተፈታኞች ምዝገባ የተጠናቀቀው ከ3ወራት በፊት መሆኑን ገልጾ በዚህ ጊዜ ውስጥ ትምህርት ያላቋረጡ እና ለፈተና ዝግጁ ናቸው የተባሉ ተማሪዎችን መዝግበን ጨርሰናል ነው ያለው፡፡
ነገር ግን ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ተመዝግበውም ሆነ ሳይመዘገቡ በተለያየ ምክንያት ፈተናው ያለፋቸው ተማሪዎች ክልሎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት ፈተናውን የሚፈተኑ ይሆናል ተብሏል፡፡
የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ከሀምሌ 3-5 ፈተናውን የሚወስዱ ሲሆን ለተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ደግሞ ከሀምሌ9-11 ፈተናው የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ባለፉት አመታት በተሰጡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎች በርካታ ተማሪዎች መውደቃቸውን ተከትሎ የፈተና አሰጣጡ እና የትምህርት ስርአቱ በርካታ ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርም የውጤቱ መወረድ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚጠቁም ነው ማለቱ ይታወሳል።
በ2015 ዓ.ም 845 ሺህ ተማሪዎች ፈተናው ላይ ተቀምጠው የማለፊያ ውጤት ወይም ከግማሽ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች 3 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ እንደሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
በአጠቃላይ በ2015 ዓ.ም ከተፈተኑ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ብዛት 27 ሺህ 267 ብቻ ናቸው።