የዘንድሮው 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሀምሌ ወር ላይ ይሰጣል ተባለ
የ2016 ብሔራዊ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ 11 ቀን እንደሚሰጥ ተገልጿል
ፈተናው በበይነ መረብ እና በወረቀት እንደሚሰጥም መንግስት አስታውቋል
የዘንድሮው 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሀምሌ ወር ላይ ይሰጣል ተባለ፡፡
የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት የ2016 የትምህርት ዘመን አገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ወይም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚሰጥበትን ቀን ይፋ አድርጓል።
እንደ ተቋሙ መግለጫ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ለማሕበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ከሐምሌ 3 እስከ 5 ቀን 2016 ይሰጣል።
የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ ከሐምሌ 9 እስከ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ይፈተናሉ የተባለ ሲሆን ፈተናው በበይነ መረብ (Online) እና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ደግሞ በወረቀት እንደሚሰጥ ተቋሙ አስታውቋል።
የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ያላለፉ ተማሪዎች እጣፋንታ ምን ይሆናል?
ፈተናውን በወረቀት የሚወስዱ የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 01 ቀን 2016 እንዲሁም የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ከሐምሌ 6 እስከ 7 ቀን 2016 ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በተመረጡ ከተሞች በኦን ላይን ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ምክክር መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በተመረጡ ከተሞች በኦንላይን እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን መስጠት ባይቻልም በሁሉም ክልሎች በተመረጡ ከተሞች ለመስጠት እየተሠራ መሆኑንም ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡
ተማሪዎች ፈተናውን ከመውሰዳቸው በፊትም የሙከራ ፈተና የሚለቀቅላቸው ሲሆን ደጋግመው እንዲሞክሩና እንዲለማመዱ እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡
በ2015 ዓ.ም 845 ሺህ ተማሪዎች ፈተናው ላይ ተቀምጠው የማለፊያ ውጤት ወይም ከግማሽ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች 3 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ እንደሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
በአጠቃላይ በ2015 ዓ.ም ከተፈተኑ ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ብዛት 27 ሺህ 267 ብቻ ናቸው የተባለ ሲሆን 19 ሺህ 17 ከተፈጥሮ ሳይንስ 8 ሺህ 250 ተማሪዎች ደግሞ ከማህበራዊ ሳይንስ ናቸው ተብሏል፡፡
649 የተፈጥሮ ሳይንስ ከፍተኛው ውጤት ሆኖ ሲመዘገብ በአዲስ አበባ ልደታ የሚገኝ ትምህርት ቤት ከፍተኛውን ውጤት ሲያስመዘገብ የማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 533 በአማራ ክልል ሐዲስ ዓለማየሁ ትምህርት ቤት መመዝገቡ ይታወሳል፡፡