በአደጋው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳትም በአደጋው ሲሞቱ መሰረተ ልማቶችም ወድመዋል
በቬትናም በተከሰተ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ የ90 ሰዎች ሀይወት አለፈ
በመካከለኛው ቬትናም በጣለ ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በተከሰቱ የጎርፍ ፣ የመሬት መንሸራተት እና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች የ90 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 34 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁንየሀገሪቱ የተፈጥሮ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከላዊ አመራር ኮሚቴ በዛሬው ዕለት አስታውቋል፡፡
121,280 ሰዎችን ከአደጋወ ስፍራ ማውጣት የተቻለ ሲሆን 121,700 ቤቶች በጎርፍ መጥለቅለቃቸውንም ኮሚቴው ገልጿል፡፡ ዶሮዎችን ጨምሮ ከ531800 ሺህ በላይ የቤት እንስሳትም በአደጋው ሞተዋል ነው የተባለው፡፡ በርካታ መሰረተ ልማቶችም መውደማቸውን የሲጂቲኤን ዘገባ ያመለክታል፡፡
በአካባቢው የሚጥለው ዝናብ ለተወሰኑ ቀናት ቀጣይነት እንደሚኖረውም በዘገባው ተገልጿል፡፡ በአንድ አንድ የመካከለኛው ቬትናም አካባቢዎች የዝናቡ መጠን ከ600 ሚ/ሜትር በላይ እንደሚሆንም ነው የተፈጥሮ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከላዊ ኮሚቴ የገለጸው፡፡
ከአደጋው ጋር ተያይዞ የአካባቢው ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡
ኮሚቴው እሁድ ጥቅምት 08 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በማዕከላዊ ቬትናም የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን ስጋት በተመለከተ ደረጃ-አራት ማስጠንቀቂያ አውጥቷል ፤ ይህም በሁለተኛ ከፍተኛ የማስጠንቀቂያ ደረጃ ላይ የሚመደብ ነው፡፡