የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረቻ ቻርተር የተፈረመበት የአዲስ አበባው አዳራሽ ሊታደስ ነው ተባለ
የተባበሩት መንግስታት ለፕሮጀክቱ 57 ሚሊዮን ዶላር በጀት አጽድቋል
አዳራሹ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ የኢሲኤ ዋና መስሪያ ቤት ሆኖ እንዲያገለግል በስጦታ የተበረከተ ነው
የአፍሪካ ታሪክ ህያው ምልክት ተደርጎ የሚወሰደው የኢሲኤ አፍሪካ አዳራሽ እድሳት ሊደረግለት መሆኑ ተገለጸ፡፡
በኢሲኤ የአፍሪካ አዳራሽ ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ አቶ ጌታቸው ካሳ ፤የአፍሪካ አዳራሽን የማዘመን እና ህንጻው ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የተከተለ መሆኑን የሚያረጋግጥ እድሳት እንደሚደረግለት ተናግረዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ይህን ያሉት “የአፍሪካ አዳራሽ እና ፓን አፍሪካኒዝም፡ ያለፈ፣ የአሁን እና የወደፊት” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ነው፡፡
አቶ ጌታቸው ካሳ በ1961 የተመረቀውንና በፓን አፍሪካኒዝም ታሪክ ውስጥ አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችበትን ጨምሮ በርካታ ጠቃሚ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት የአፍሪካ አዳራሽ ያለውን ታሪካዊ ፋይዳ እጅግ የላቀ መሆኑም ገልጸዋል፡፡
“አዳራሹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ወደ አፍሪካ የመሳብ እና የአፍሪካ መንግስታትን የማዋሀድ ራዕይ ያለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ የኢሲኤ ዋና መሥሪያ ቤት ሆኖ እንዲያገለግል ተወስኖ በስጦታ የተበረከተ ነው” ብለዋል አቶ ጌታቸው፡፡
በተጨመሪም አዳራሹ በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) የምስረታ ቻርተር የተፈረመበት ታሪካዊ ስፍራ ነው ብለዋል፡፡
በኢሲኤ የአፍሪካ አዳራሽ የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አንቶኒ ቢያኦ በበኩላቸው፤ የአዳራሹን በዘመነ እና የቴክኖሎጂ ፋሲሊቲዎች ባሟላ መልኩ የማደስ አስፈላጊነት አስምረውበታል።
እድሳቱ የመሬት መንቀጥቀጥ መቋቋም በሚያስችል እና የህንታውን ተደራሽነት በሚያሻሽል መልኩ የሚደረግ ነው ያሉት አንቶኒ ቢያኦ ፤ ትልቁ ራእይ ዘመናዊ፣ የጎብኚዎች ማእከል እና ቋሚ የኤግዚቢሽን ቦታ መፍጠር ነው ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት እንደፈረንጆቹ በ2015 ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤው ለፕሮጀክቱ 57 ሚሊዮን ዶላር በጀት ማጸደቁም ተናግረዋል፡፡
አንቶኒ ቢያኦ እንዳብራሩት እድሳቱ “የአፈወርቅ ተክሌ ባለቀለም መስታወት ትሪፕቲች-የአፍሪካ አጠቃላይ ነጻ አውጪ” - እና ዋና ዋና ባህሪያትን ጨምሮ ለስነ ጥበብ ስራዎች እና ምልክቶች ልዩ ትኩረት የተሰጣቸውን ጨምሮ ኦርጅናል የንድፍ መርሆዎችን አይነካም ብለዋል ፡፡
“የማሻሻያ ፕሮጀክቱ የአፍሪካን ታሪክ እና ባህል ለመጠበቅ ጠቃሚ በመሆኑ በተለይ ከአፍሪካ አባል ሀገራት የበጎ ፈቃደኝነት አስተዋጽኦ ያድርጉ” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአፍሪካ አዳራሽ የእድሳት ስራ እንደፈረንጆቹ በጥቅምት 14 ቀን 2022 የሚጀመር ሲሆን በ2024 አጋማሽ ይከፈታል ተብሎ ይጠበቃል።