ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ያቀረበውን የድርድር ጥሪ መቀበሏን አስታወቀች
የአፍሪካ ህብረት የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ድርድራቸውን እንዲጀምሩ ሲያሳስብ ቆይቷል
ህብረቱ ሁለቱ አካላት የድርድር ቦታ እና ቀን እንዲያሳውቁ ጥሪ አቅርቧል
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ከህወሀት ጋር በሚደረገው ድርድር ዙሪያ ያቀረበውን ጥሪ ተቀበለች።
የፌደራል መንግስትና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ እንደሚደራደሩ ሲጂቲኤን ዘግቧል።
የአፍሪካ ኅብረት ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት የሰላም ንግግሩን የሚመሩ አካላትን፤ ቀንና ስፍራን አሳውቆ የሰላም ውይይቱ እንዲጀመር በይፋ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
የፌደራል መንግሥት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ባወጣው መግለጫ የአፍሪካ ህብረት የድርድር ጥሪን እንደተቀበለ አስታውቋል።
የአፍሪካ ኅብረት ግብዣ መንግሥት ከዚህ በፊት ያቀረባቸውን አቋሞች የጠበቀ ሆኖ ተገኝቷል ያለው የፌደራል መንግስት ንግግሩ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ብቻ እንዲሆንና ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲደረግ መንግሥት አቋሙን ሲገልጥ መቆየቱ አስታውቋል።
ግጭቱን ለመፍታት መንግሥት ሁሉንም ዓይነት የመፍትሔ ርምጃዎች ለመውሰድ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን የጠቆመው የፌደራል መንግስት መግለጫ አሁንም ጥረቴን አቀጥላለሁ ብሏል።
የፌደራል መንግስት በበኩሉ ህወሓት የሰላም መንገዶችን ሁሉ በመዝጋት ከነሀሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አማራ ክልል እና አፋር ክልል ጦርነት መክፈቱን ተናግሮ ነበር።
ከዚህ ጊዜ አንስቶም በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በኢትዮ ሱዳን ድንበር፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ጦርነት እየተካሄደ እንደነበር የፌደራል መንግስት ከዚህ በፊት በሰጣቸው መግለጫዎች ላይ አስታውቋል።
የድርድር ጥሪው ከፌደራል መንግስቱ በተጨማሪ ለህወሓትም ሮይተርስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ህወሓት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነቱ ድጋሚ ከተቀሰቀሰ በኋላ በአፍሪካ ህብረት ስር ለሚደረገው ድርድር ዝግጁ መሆኑን ግልጽ አድርጓል።
ጦርነቱ በነሀሴ ወር ከመቀስቀሱ በፊት በአፍሪካ ህብረት የአደራዳሪነት ሚና ላይ ጥያቄ ሲያነሳ የነበረው ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ስር ለመደራደር እንደሚፈልግ ከሳምንት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።