አለምአቀፉ ማህበረሰብ በንጹሀን የአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ችላ ብሎታል-የአማራ ማህበር በአሜሪካ
ማህበሩ በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ ከታወጀ አንስቶ እስካሁን የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተባብሶ ቀጥሏል ሲል ወቅሷል
ማህበሩ በአንድ አመት ውስጥ በተፈጸሙ 200 ጥቃቶች ከ3ሺ በላይ ንጹሀን ላይ ጉዳት ደርሷል ብሏል
አለምአቀፉ ማህበረሰብ በንጹሀን የአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ችላ ብሎታል ሲል የአማራ ማህበር በአሜሪካ ወቅሷል።
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ለአማራ መብት የሚሟገተው ማህበሩ ትናንት መስከረም 7፣ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በአንድ አመት ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን አማራዎች ተገድለዋል ብሏል።
ማህበሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ሀምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል እና የአማራ ተወላጆች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚፈጠሩ ጥሰቶች መጠናቸው በመጨመር ላይ እንደሚገኝ የተለያዩ ሪፖርቶች ቢያመላክቱም አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው ብሏል።
ከተለያዩ አለም አቀፍ እና ከሀገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ባለሙያዎችን መሰረት አድርጎ አሰባሰብኩት ባለው መረጃ የሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ ያለ ፍርድ የሚደረጉ የዘፈቀደ እስር ፣ግድያዎች እንዲሁም እገታ እና ሌሎችም ጥሰቶች የመንግስት የጸጥታ ሀይሎችን ጨምሮ በተለያዩ አካላት እንደሚፈጸም አመላክቷል፡፡
ሪፖርቱ ከኅምሌ 28 ቀን 2015 እስከ ኅምሌ 28 ቀን 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎች አካባቢዎች በ16 ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ጭምር በመጠቀም ጥቃት ተፈጽሟል ነው ያለው፡፡
የመንግስት የጸጥታ ኃይሎችን ፣ መንግስት ሸኔ ብሎ በሽብር የፈረጀውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና የትግራይ ሀይሎችን ተጠያቂ ባደረገባቸው "200 ጭፍጨፋዎች" በ3,283 ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን 2,592 ንፁሀን ዜጎች መገደላቸውን እና 691 መቁሰላቸውን ዘርዝሯል፡፡
ማህበሩ አክሎም በክልሉ ቢያንስ 53 የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸውን የ433 ሰዎችን ህይወት መቅጠፋቸውን ገልጿል።
በ138 ገጽ ሪፖርቱ የተጎጂዎችን ስም እና ፎቶ እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸውን ስፍራዎች በስም ዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን፤ ተፈጽመዋል ካላቸው ጥሰቶች መካከል 269 ሰዎች ተገደው መደፈራቸውን የዚህ ወንጀል ሰለባዎች አብዛኛዎቹ ወጣት ልጃገረዶችና ሴቶች እንደሆኑም አመላክቷል፡፡
በትምህርትና በጤና ተቋማት ላይ ደርሷል ባለው ጥቃት ከ4.1 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በትምህርት ገበታቸው መለያየታቸውን፣ ከ4,178 በላይ ትምህርት ቤቶች በክልሉ መዘጋታቸውን ዳሷል፡፡
ማህበሩ በዋናናት ተፈጸመዋል በሚል ከዘረዘራቸው ዋና ዋና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል "በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የአማራ ተወላጆች ፋኖን ይደግፋሉ ወይም ለፋኖ ይሰልላሉ" በሚል ከስራ ይባረራሉ ሲል ከሷል፡፡
በክልሉ ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ተመሳሳይ በደሎች ከአዲስ አበባ ባለፈ በሌሎች አካባቢ በሚኖሩ ተወላጆች ላይም ያነጣጠረ ነው ያለው ሪፖርቱ ፤ የዘፈቀደ የማስቆም እና መፈተሽ ተግባር፣ አስገድዶ ገንዘብ መቀበል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የብሄረሰቡ ተወላጆች የጅምላ እስር፣ የእስረኞች አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃት፣ ቤተሰብ እንዳይጎበኝ መከልከል፣ የበቂ ህክምና አገልግሎት መነፈግ እና ንጽህናቸው ባልጠበቀ ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ ይገደዳሉ ነው ያለው፡፡
ማህበሩ አደረኩት ባለው ዳሰሳ የቴሌኮሙዩኒኬሽን መቆራረጥ እና በቦታው ያለው የጸጥታ ችግር ምርመራውን በጥልቀት ለማካሄድ አስቸጋሪ ስላደረጉት የትክክለኛውን የጥቃት መጠን አነስተኛ ክፍል ብቻ እንደሚያሳዩ ገልጿል።
እየተካሄደ የሚገኝውን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ቢኖሩም ምዕራባውያን መንግስታት እየተፈጸመ ያለውን በደል ለማስቆም እና ለማውገዝ ዳተኝነት አሳይተዋል ሲል ከሷቸዋል፡፡
ማህበሩ አይኤምኤፍን ሌሎች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ምንጮችን ለኢትዮጵያ መንግሥት ዕርዳታና ብድር በማቅረብ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ እንዲቀጥሉ ደግፈዋልም የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል።
ማህበሩ በአማራ ክልል እና በሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየደረሰ ያለውን በደል ለማስቆም እና ተጨማሪ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ለማድረግ በመንግስት ላይ ግፊት ማድረግ የሚችሉ አልም አቀፍ አካላት ሁሉ እርምጃ እንዲወስዱ በማጠቃለያው ጠይቋል፡፡
በአማራ ክልል በመንግስታ የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው የትጥቅ ግጭት ከአንድ አመት በላይ አስቆጥሯል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን(ኢሰመኮ) ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ በክልሉ በግጭቱ አውድ ውስጥ እና ውጭ በንጽሀን ግድያን ጨምሮ የመብቶች ጥሰት ተባብሷል ብሏል።
መንግስት ለእንዲህ አይነት ሪፖርቶች በአብዛኛው መልስ የማይሰጥ ቢሆንም የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባለፈው አመት ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቆይታ በክልሉ ህዝብን በማይጎዳ መልኩ ታጣቂዎቹን ኢላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸው ይታወሳል።