ጣሊያናዊው የ1990 የአለም ዋንጫ ኮከብ ስኪላቺ ህይወቱ አለፈ
“ቶቶ” በሚል ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው ሳልቫቶር ስኪላቺ በካንሰር ህመም ነው በ59 አመቱ ህይወቱ ያለፈው
ስኪላቺ ለጁቬንቱስና ኢንተርሚላን የተጫወተ ሲሆን ክለቦቹና የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር የሀዘን መግለጫ አውጥተዋል
በ1990ኙ የአለም ዋንጫ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ጣሊያናዊው አጥቂ ሳልቫቶር ስኪላቺ ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል።
በ2022 በካንሰር የተጠቃው ስኪላቺ በ59 አመቱ ይህቺን አለም መሰናበቱን የጣሊያን መገናኛ ዘግበዋል።
“ቶቶ” በሚል አጭር ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው ስኪላቺ ጣሊያን ባዘጋጀችው የአለም ዋንጫ ስድስት ጎሎችን በማስቆጠር ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የወርቅ ጫማ ተሸልሟል።
ስኪላቺ በ1990ው የአለም ዋንጫ የመጀመሪያዋን ጎል ያስቆጠረው ከኦስትሪያ ጋር በተደረገ ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ ነው።
ሮቤርቶ ባጆን ከፊት ባሰለፈው የጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ከተጠባባቂነት ተነስቶ ግብ ያስቆጠረው “ቶቶ” በሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች በኡራጓይ እና አየርላንድ ላይ ጎሎችን በማስቆጠር ወሳኝ ተጫዋችነቱን አሳይቷል።
በግማሽ ፍጻሜውም ከአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ጋር በተደረገው ጨዋታ ግብ ቢያስቆጥርም አዙሪዎቹ ለፍጻሜ አልደረሱም። ስኪላቺ ግን ከእንግሊዝ ጋር ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ ግብ በማስቆጠር የውድድሩ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ክብርን መቀዳጀቱ የሚታወስ ነው።
ለሀገሩ 16 ጊዜ ተሰልፎ ሰባት ጎሎችን ያስቆጠረው ስኪላቺ ለጁቬንቱስ እና ኢንተርሚላን ተጫውቷል።
ጁቬንቱስ “ቶቶ በ1989 ሲቀላቀለን ደስታችን ወደር አልነበረውም፤ ትጋቱ፣ የኳስ ፍቅሩና ታሪኩ አስገራሚ ነው፤ በ1990ው የአለም ዋንጫ ጎል ካስቆጠረ በኋላ የሚያሳየው የደስታ አገላለጽም ከጣሊያናውያን አዕምሮ አይጠፋም” በሚል በህልፈቱ ከባድ ሀዘን እንደተሰማው ገልጿል።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒም “በጣሊያናውያን እና በመላው የአለማችን እግርኳስ አፍቃሪ ልብ ውስጥ የገባው የእግርኳስ ፈርጥ አሁን አርፏል” ብለዋል።
የሴሪ አ ፕሬዝዳንቱ ሎሬንዞ ካሲኒም ስኪላቺ “በእግርኳስ መድረክ ገኖ የመውጣት ብርቱ ጥረቱ ለበርካቶች መነሳሻ ሆኖ ሁሌም ሲወሳ ይኖራል” ማለታቸውን ዩሮ ኒውስ አስነብቧል።
ስኪላቺ ከ1990ው የአለም ዋንጫ በኋላ ለሀገሩ አንድ ግብ ካስቆጠረ በኋላ በትልልቅ መድረኮች አልተሰለፈም።
በ1999 ጫማ ከመስቀሉ በፊትም በጃፓን “ጄ ሊግ” የተጫወተ የመጀመሪያው ጣሊያናዊ ተጫዋች ነበር።