በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በተራዘሙ ግጭቶች ምክንያት የሚፈጸሙ እገታዎች ተባብሰው ቀጥለዋል -ኢሰመኮ
ኢሰመኮ ባወጣው ሪፖርት እገታዎቹው ለዘረፋ "በተደራጁ ቡድኖች እንዲሁም በአንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላት" የሚፈጸሙ ናቸው ብሏል
መንግስት የተራዘሙ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት እና ተደጋጋሚ እገታዎች በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ትኩረት እና የደህንነት ከለላ እንዲሰጥ አሳስቧል
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በተራዘሙ ግጭቶች ምክንያት የሚፈጸሙ እገታዎች ተባብሰው መቀጠላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከተራዘሙ የትጥቅ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የሕግ ማስከበር እና የመንግሥት መዋቅር መላላት ሳቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ እገታዎች መባባሳቸውን ብሏል ኢሰመኮ፡፡
ኢሰመኮ አደረኩት ባለው ማጣራት ለዘረፋ "በተደራጁ ቡድኖች እንዲሁም በአንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላት አባሎች" እገታዎች እንደሚፈጸሙ ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡
አጋቾች ሰላማዊ ሰዎችን በአብዛኛው በጉዞ (ትራንስፖርት) ላይ እያሉ አንዳንዴም ከመኖሪያ ቤታቸው ወይም ከሥራ ቦታቸው አግተው ወዳልታወቀ ቦታ በመውሰድ ከፍተኛ የማስለቀቂያ ገንዘብ ክፍያ እንደሚጠይቁ ፤ ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ በርካታ ታጋቾች ግድያን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ እንደሚገኙ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
እገታው በተደጋጋሚ በተደራጀ መልኩ የሚፈጸም ነው ያለው ኢሰመኮ "እንደ ገቢ ማስገኛ ፣ እንደ በቀል ማስፈጸሚያ፣ ለፖለቲካ ዓላማ ወይም የታገተ ሌላ ሰውን ለማስለቀቅ" በሚል በአጸፋ መልኩ የሚፈጸም ነው ተብሏል፡፡
እነዚህ እገታዎች ጾታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት፣ የንብረት መብት እና የመዘዋወር ነጻነት ላይ ጥሰት ማድረሳቸውን የገለጸው ኢሰመኮ በዚህ አይነት መንገድ የሚገኝ ገንዘብ ለመሣሪያ ግዢ ሊውል የሚችል ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ግጭቶቹን ሊያራዝም እንዲሁም ግጭቶቹን በዘላቂነት ለማስቆም በሚደረገው ድርድር ተግዳሮት ሊሆን ይችላል ነው ያለው።
ኢሰማኮ ከዘረዘራቸው እገታዎች መካከል ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ ከተማ አካባቢ የተፈጸመው አንዱ ነው፡፡
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት በሚጠራው ቡድን (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’) ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበሩ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችን በማስቆም በአብዛኛው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሆኑ መንገደኞችን አግተው ወስደዋል።
ከነዚህ ውስጥ 3 ተማሪዎች እስከ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ እያንዳንዳቸው 150,000 ብር ከፍለው መለቀቃቸውን፣ አንድ ተማሪ ደግሞ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. የተጠየቀችው 400,000 ብር ከተከፈለ በኋላ ወደ ገበያ ከሚሄዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ተቀላቅላ እንድትወጣ መደረጉን እና ወደ አዲስ አበባ መምጣቷ ተነግሯል፡፡
አሁንም ታግተው ያሉ ተማሪዎች ብዛት ስንት እንደሆነ በውል እንደማይታወቅ እና ተማሪዎች ከአውቶብሶቹ ከወረዱ በኋላ በተለያየ ቡድን ተከፋፍለው የተወሰዱ በመሆኑ ታጋች ተማሪዎች እራሳቸው ከነበሩበት ቡድን ውስጥ የቀሩትን ታጋቾች ብዛት እንጂ ሌላውን ቡድን ስለማያውቁ አጠቃላይ ብዛቱን እንደማታውቅ ኢሰመኮ ያነጋገራት ታግታ የተለቀቀች ተማሪ አስረድታለች።
የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ‘በሕዝብ እና መንግሥት የተቀናጀ ኦፕሬሽን’ ከታገቱት 167 ተማሪዎች መካከል 160 የሚሆኑትን ማስለቀቅ መቻሉን ገልጿል።
ሆኖም እገታው ከተፈጸመ በኋላ ታጣቂዎቹ ታጋቾችን ወደ ተለያዩ ቡድኖች በመከፋፈል ወደ ገጠራማ አካባቢዎች ይዘው የገቡ በመሆኑ ምስክሮች በነበሩበት ቡድን ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ከማስረዳት ባለፈ በሌሎች ቡድኖች ውስጥ የነበሩ ታጋቾችን ሁኔታ ሊያውቁ የማይችሉ በመሆኑ በአጠቃላይ የታገቱ፣ ገንዘብ ከፍለውም ሆነ ሳይከፍሉ የተለቀቁ እንዲሁም በወቅቱ በነበረ የተኩስ ልውውጥም ሆነ ከዚያ በኋላ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጥረት የተለቀቁ ተማሪዎችን ቁጥር መለየት አስቸጋሪ መሆኑን ማወቅ ተችሏል።
በተመሳሳይ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ልዩ ስሙ ቱሉ ሚልኪ በሚባል አካባቢ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት የሚጠራው ቡድን (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’) ታጣቂዎች በጉዞ ላይ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ በማስቆም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ መንገደኞችን አግተው የወሰዱና ሹፌሩና ረዳቱን የገደሏቸው መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
ኢሰመኮ በዚህ ጉዳይ ዝርዝር ሁኔታዎችን ለማወቅ የሚያደርገውን ምርመራ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡
የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደብረሊባኖስ ወረዳ ባቡ ኢተያ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ሕፃናት፣ ሴቶች እና አረጋውያንን ጨምሮ 20 ሰዎች ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት በሚጠራው ቡድን ታጣቂዎች ታግተው ተወስደዋል፡፡
18 ሰዎች እስከ ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ በመክፈል መለቀቃቸውን እንዲሁም 2 ታጋቾች ከግንቦት 10 እስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እያንዳንዳቸው 120,000 ብር በመክፈል መለቀቃቸውን ለማወቅ ተችሏል።
አማራ ክልል የተፈጸሙ እገታዎችን አስመለክቶ ኢሰመኮ ከጠቀሳቸው መካከል ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ ‘ፋኖ’) “መከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው ሲገባ መንገድ አሳይታችኋል፤ ሰዎችን ጠቁማችሁ አስይዛችኋል በማለት 17 የአካባቢው ነዋሪዎችን ይዘው ገርጨጭ ከተማ ውስጥ አንበርክከው እንዲጓዙ እንዳደረጓቸው፤
በማግስቱ ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ከእነዚህ ውስጥ 4 ሰዎች (1 ሴት እና 3 ወንዶች (2 የሀገር ሽማግሌዎችና 1 የወረዳው ቤተ ክህነት ተወካይ ቄስ)) ተገድለው አስከሬናቸው ተጥሎ እንደተገኘ እና የቀሩት ሰዎች ደግሞ ገንዘብ በመክፈል ከቀናት በኋላ እንደተለቀቁ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ የአማራ ክልል አድማ ብተና ዩኒፎርም የለበሱ ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ሰዎች በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3 ሠራተኞችን በየመኖሪያ ቤታቸው በመሄድና በማገት በፒካፕ መኪና ጭነው ከወሰዷቸው በኋላ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 16 በሚገኘው ሜዳ ላይ እጅ እና እግራቸውን ታስረው ተጥለው መገኘታቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. "Action for Social Development and Environmental Protection Organization (ASDEPO)" የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት 4 ሠራተኞች በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ኩርባ ከተማ ከተኙበት ክፍል በታጠቁ ሰዎች በሌሊት ታፍነው መወሳዳቸው ተገልጿል፡፡
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ባወጣው መግለጫ፤ “የኃይል አማራጭን እንደ መፍትሔ የወሰደው ታጣቂ ቡድን ሀገረ መንግሥትን በኃይል ከመናድ ጀምሮ አድማሱን እያሰፋ ንፁሃንን ዒላም በማድረግ ከማገትና የሀብት ማጋበሻ መንገድ አድርጎ ከመጠቀም ባለፈ የለጋ ህፃናትን፣ ህይወት ጭምር እየቀጠፈ ይገኛል” ብሏል
“እየተፈፀመ ያለው አስነዋሪ ድርጊት አሳዛኝና ሆን ተብሎ ታቅዶ የሚፈፀም የጠላት አጀንዳ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል” ብሏል።
“የእገታ ድርጊት ተባባሪ ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩ 14 የፀጥታ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያጣራን እንገኛለን” ሲል አስታውቋል።