አልጄሪያን ይዘውሩ ነበር የተባሉት የአብዱላዚዝ ቡተፍሊካ ታናሽ ወንድም ሌላ ክስ ተመሰረተባቸው
ሰኢድ ቡተፍሊካ ፕሬዚዳንቱ ህመም ላይ ሳሉ የሀገሪቱ አድራጊ ፈጣሪ ነበሩ ተብሏል
በሀገርና በጦሩ ላይ አሲረዋል ከሚለው ክሳቸው ነፃ ቢሆኑም አዲስ የሙስና ክስ ቀርቦባቸዋል
በአውሮፓውያኑ 2019 በነበረው የአልጄሪያውያን የአደባባይ ተቃውሞ ፣ ከቤተ መንግስት የተሰናበቱት የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ ታናሽ ወንድም ሰኢድ ቡተፍሊካ ከተመሰረተባቸው ክስ ነጻ መውጣታቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
በሀገርና በጦሩ ላይ አሲረዋል በሚል በ2019 የ 15 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው የነበሩት ሰኢድ ቡተፍሊካ ክሳቸው ተነስቶላቸዋል፡፡ ግለሰቡ አልጄሪያውያን ዴሞክራሲን የሚያበረታታ ተቃውሞ ሲያደርጉ እንቅፋት ሆነው ነበር ፤ በጦሩ እና በሀገራቸው ላይም አሲረዋል ተብለው የነበረ ቢሆንም ከዚህ ክስ ነጻ ተደርገዋል፡፡
ይሁንና ሰኢድ ቡተፍሊካ ከዚህ ክስ ነጻ ቢሆኑም የሙስና ክስ እንደሚጠብቃቸው ሜይል ኦን ላይን ዘግቧል፡፡የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከ 2013 ጀምሮ ህመም ላይ ሳሉ ሀገሪቱን ሲዘውሩ የነበሩት ሰኢድ ቡተፍሊካ ታስረው ፣ የነበሩት ከሁለት የቀድሞ የደህንነት ኃላፊዎች ጋር ነበር፡፡
ሰኢድ ቡተፍሊካና ሁለት ጓዶቻቸው በታሰሩ ጊዜ የሀገሪቱ ፖለቲካ አዋቂዎች አዲሱ መንግስት ሙስናን ለማስቆም ቆርጦ ተነስቷል ፣ የሚል ሀሳብ ሰንዝረው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በፈረንጆቹ ሕዳር 2020 የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አንደገና በማየት ሦስቱም ነጻ እንዲሆኑ አዞ የነበረ ሲሆን ሰኢድ ቡተፍሊካ ግን ወደ ሌላ እስር ቤት በመሄድ የሙስና ክሳቸውን ይከታተላሉ፡፡