አቡበከር ናስር የማሜሎዲ ሰንዳውን ዝውውሩን ለማጠናቀቅ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዟል
ባሳለፍነው ጥር ወር ማሜሎዲን ለመቀላቀል የሚያስችለውን ቅድመ ስምምነት ውል ማሰሩ ይታወሳል
አቡበከር የምጊዜውም የፕሪሚዬር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አግቢ ነው
የኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ ብሐየራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) አጥቂ አቡበከር ናስር ወደ ደቡብ አፍሪካው ኃያል እግር ኳስ ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውን የሚያደርገውን ዝውውር ለማጠናቀቅ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዟል፡፡
አቡበከር ናስር ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናቱን የተለያዩ የሃገር ውስጥ እና የደቡብ አፍሪካ የስፖርት ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
ተጫዋቹ ባሳለፍነው ጥር ወር ማሜሎዲን ለመቀላቀል የሚያስችለውን ቅድመ ስምምነት ውል ያሰረ ሲሆን ውሉን በማጠናቀቅ ኮንትራት ለመፈራረም ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናቱ ነው የተነገረው፡፡
በዚያ በመኖረው ቆይታ ሙሉ በሙሉ የሰንዳውን ተጫዋች ሊሆን የሚችልበትን ኮንትራት አጠናቆ እንደሚመለስ ይጠበቃል፡፡
ትናንት ኢትዮጵያ ቡና በባህር ዳር አለም አቀፍ ስታዲየም ከአዲስ አበባ ጋር ባደረገው የ27ኛ ሳምንት ቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ የአቻነቷን ጎል በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረው አቡበከር የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የምን ጊዜም ኮከብ ግብ አስቆጣሪም ይኸው ተስፈኛ ወጣት ተጫዋች ነው፡፡
አቡበከር በዚህ የውድድር ዓመት ለቡናዎቹ ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች 14 ጎሎችን ሲያስቆጥር 5 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡
ማሜሎዲ በዚህ የአቡበከር ግብ የማስቆጠር አቅም እና የጨዋታ ክህሎት መማረኩ ነው የተነገረው፡፡
ዝውውሩ ተሳክቶ የሚጠናቀቅ ከሆነ አቡኪ በቀጣዩ የውድድር ዓመት በደቡብ አፍሪካ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወት ይሆናል፡፡