“ለጉዞ እና ለልምምድ የሚሆን በቂ ጊዜ ባለመኖሩ በማላዊ መጫወትን መርጠናል”- አቶ ኢሳያስ ጅራ
አቶ ኢሳያስ ማላዊ ሜዳዋን በመፍቀዷ ሊከፈል የሚችል ገንዘብ መኖሩን ጠቅሰው መጠኑን ከመግለጽ ተቆጥበዋል
“ኢትዮጵያ በማላዊ ለመጫወት በመወሰኗ የሊቨርፑል ደጋፊዎች መሃመድ ሳላህ ከዋሊያዎቹ ሲጫወት የሚመለከቱበትን ዕድል ያገኛሉ” - የማላዊ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት
ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ያላትን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ በማላዊ ሊሎንግዌ ነው የምታደርገው ተባለ፡፡
የማጣሪያ ጨዋታው ሊሎንግዌ በሚገኘው ቢንጉ ብሔራዊ ስቴዲየም እንደሚደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ዋሊያዎቹ ከሜዳቸው ውጭ በገለልተኛ ሃገር የሚጫወቱት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ባህር ዳር ስቴዲየም ዓለም አቀፍ አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ብቁ አይደለም ማለቱን ተከትሎ ነው፡፡
ስቴዲየም የካፍን ዝቅተኛ መስፈርቶች አሟልቶ ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው በደጋፊዎቹ ፊት እንዲጫወት ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም፡፡
ካፍ ከአሁን ቀደምም የማሻሻያ ምክረ ሃሳቦችን በመስጠት ስቴዲየሙን አግዶ ነበር፡፡ በምክረ ሃሳቦቹ መሰረት ስቴዲየሙን ከግብጽ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ለማዘጋጀት ጥረቶች ሲደረጉም ነበረ፡፡ በጥረቱ የተሻለ ነገር ለመስራት ስለመቻሉ ራሱ ካፍ የላካቸው ሰዎች ስለመገምገማቸው ቢነገርም ጥረቱ ፍሬ ሳያፈራ ቀርቶ ብሔራዊ ቡድኑ ከሜዳው ውጭ ለመጫወት ተገዷል፡፡
ካፍ ቢንጉ ብሔራዊ ስቴዲየምን በጊዜያዊነት ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ይችላል የሚል ፈቃድ በመስጠቱ ነው ማላዊም በሜዳዊ የምትጫወተው፡፡
ማላዊ በምን መስፈርት ልትመረጥ እንደቻለች አል ዐይን አማርኛ በስልክ የጠየቃቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ የተጫዋቾቹን ድካምና እንግልት፣ የልምምድ ጊዜ እንዲሁም ወጪን ለመቀነስ በማሰብ መመረጧን ገልጸዋል፡፡
ዋሊያዎቹ የመጀመሪያ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ከራሷ ከማላዊ ብሔራዊ ቡድን ጋር በዚያው በቢንጉ ዓለም አቀፍ ስቴዲየም ነው፡፡
ከማላዊ ጋር የሚኖረው የመክፈቻው ጨዋታ ግንቦት 25 የሚካሄድ ሲሆን ከቀናት በኋላ ግንቦት 29 ደግሞ ዋሊያዎቹ ከፈርዖኖቹ ጋር ይጫወታሉ፡፡
"ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው ከተጫወተ ሁለት ዓመት አልፎታል እና በባህርዳር የሚጫወት ከሆነ በጣም ትልቅ አድቫንቴጅ አለው" - ውበቱ አባተ
ይህ ከማላዊ ውጭ በሌላ ሃገር ለመጫወት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ነው "በመካከል ያሉት ቀናቶች አጭር ናቸው" የሚሉት አቶ ኢሳያስ የሚገልጹት፡፡
በመጀመሪያውና በሁለተኛው ጨዋታ መካከል የሚኖሩት ቀናት ከማነሳቸው የተነሳ ዋሊያዎቹ ወደ ሌላ ሃገር ተጉዞ ለመጫወትም ሆነ ልምምድ ለማድረግ እንደሚቸገሩም ተናግረዋል፡፡
ደቡብ አፍሪካን እንደ ሁለተኛ አማራጭ ለማየት ሞክረን ነበር የሚሉት ፕሬዝዳንቱ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ችግሮችና ከወጪ አንጻር በሊሎንግዌ ለመጫወት መወሰናቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ለዚህም ጥሩ ግንኙነት አለን ያሉት የማላዊ እግር ኳስ ማህበር ጥያቄያቸውን በመቀበል ፈጣን ምላሽ እንደሰጣቸውና ካፍም ውሳኔውን እንደተቀበለው ገልጸዋል፡፡
አቶ ኢሳያስ ማላዊ ሜዳዋን በመፍቀዷ ሊከፈል የሚችል ገንዘብ መኖሩን ጠቅሰው መጠኑን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቢንጉ ስቴዲየም ከግብጽ ለመጫወት ስለመወሰኗ በፌስቡክ ገጻቸው የጻፉት የማላዊ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ዋልተር ኒያሚላንዱ ማንዳ ጨዋታው በሃገሪቱ የሚገኙ የሊቨርፑል ደጋፊዎች መሃመድ ሳላህን ሲጫወት ለመመልከት የሚችሉበትን አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
ሞ ሳላህ ከዋሊያዎቹ በተጨማሪ መስከረም ላይ ከሃገራቸው ብሔራዊ ቡድን “ነበልባሎቹ” ጋር ሲጫወት የማየቱን እድሉን እንደሚያገኙም ጽፈዋል፡፡
ዘመናዊ ስቴዲየምን የመገንባት ጥቅም ይህ ነው በሚልም ሃገራቸውን አወድሰዋል ዋልተር ኒያሚላንዱ ፡፡
ዋሊያዎቹ በደቡብ አፍሪካ ቢጫወቱ ደጋፊዎችን ሊያገኙ ይችሉ ነበር በሚል ፌዴሬሽኑ ማላዊን መምረጡ አግባብ አይደለም በሚል ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡም ሲሆን ደቡብ አፍሪካ መጫወቱ ከጊዜና ከወጪ አንጻር ከባድ እንደሆነ፤ ከአሁን ቀደም ከጋና ጋር የነበረው ጨዋታ ከደጋፊ ውጭ በዝግ ስታዲየም መደረጉን አንስተዋል፡፡
ዋሊያዎቹ በማላዊ እንዲጫወቱ የተወሰነው ከብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በመነጋገር እንደሆነም ነው አቶ ኢሳያስ የተናገሩት፡፡
አል ዐይን አማርኛ ብሔራዊ ቡድኑ በገለልተኛ ሜዳ መጫወቱ በቡድን ደረጃ ሊኖረው ስለሚችለው ተጽእኖና ስለ ውሳኔው አሰልጣኝ ውበቱ አባተን በስልክ አግኝቶ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
አሰልጣኝ ውበቱ ባሳለፍነው ሳምንት ብሔራዊ ቡድኑ በባህርዳር በደጋፊው ፊት ቢጫወት "በጣም ትልቅ አድቫንቴጅ" እንደሚኖረው ከስታዲየሙ የግምገማ ሂደት ጋር በተያያዘ ለጠየቃቸው ለአል ዐይን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ ኮትዲቯር ወደምታዘጋጀው የ2023ቱ የቶታል ኢነርጂ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ አራት መደልደሏ ይታወሳል፡፡ ማላዊ እና ግብጽን ጨምሮ ከጊኒ ጋር ከምድቡ ለማለፍ የምትጫወትም ይሆናል፡፡