“የሴኔጋላውያን ፍላጎት ከሆነ ሊቨርፑልን እለቃለሁ”- ሳዲዮ ማኔ
ሳዲዮ ማኔ ሊቨርፑልን እለቃለሁ ማለቱን ተከትሎ በርካታ የሊቨርፑል ደጋፊዎች መከፋታቸው እየተገለጸ ነው
ማኔ በሊቨርፑል ቆይታው በ269 ጨዋታዎች 120 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ድንቅ ተጨዋች ነው
ሴኔጋላዊ እግር ኳስ ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ ሳዲዮ ማኔ ከእንግሊዙ አንጋፋ ክለብ ሊቨርፑል ጋር በቅርቡ ሊለያይ እንደሚችል ፍንጭ ሰጠ።
ማኔ ከሊቨርፑል ሊወጣ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠው የሰኔጋል ብሄራዊ ቡድን ለ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከቤኒን አቻው ጋር የሚያደረገውን ጨዋታ በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው።
ማኔ ከቤኒን ጋር በነበረው ጨዋታ ሶስት ግቦች በማስቆጠር ሰኔጋል ቤኒንን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፋ እንድትወጣ አስችሏታል።
ሰኔጋላዊው ኮከብ ለሀገሩ በተሰለፈባቸው 86 ጨወታዎች 32 ግቦችን በማስቆጠር በሀገሪቱ ብሄራዊ ቡድን ታሪክ ከፍተኛ ግብ ያስቆጠረ ተጨዋች ለመሆን ችሏል።
ማኔ እንግሊዙ ክለብ ሊቨርፑል ጋር ያለው ውል ገና አንድ ዓመት የቀረው ቢሆንም፤ ወደ ጀርመኑ ኃያል ክለብ ባየር ሙኒክ ሊያቀና እንደሚችል መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል።
ማኔ ከቤኒን ጋር ከተደረገው ጨዋታ በፊት በሰጠው አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ሴኔጋላውያን ደጋፊዎቹ በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሚያቀርቡለትን ምክር ሊሰማ እንደሚችል በቀልድ መልክ ጣል አድርጓል።
"ከ60 እስከ 70 በመቶ ሴኔጋላውያን ከሊቨርፑል እንድወጣ ይፍልጋሉ አይደል…? ስለዚህም የሚፈልጉትን አደርጋለሁ" ሲልም ተደምጧል።
ማኔ " አታስቡ ፤ጊዜው ሩቅ አይሆንም፤ በቅርቡ የምታዩት ይሆናል" ሲልም አክሏል።
የሳዲዮ ማኔ መግለጫ በመላው ዓለም የስፖርት መገናኛ ብዙሃን መሰራጨቱን ተከትሎ፤ የሊቨርፑል ደጋፊዎች በአስታየየቱ እንደተከፉም እየተገለጸ ነው።
ማኔ በበኩሉ ደጋፊዎቹን “ይቅርታ እናንተን ለማስከፋት ፈልጌ አልነበረም ፤ ለሊቨርፑል ትልቅ ክብር አለኝ” ማለቱን ደይሊ ኦንላይን ዘግቧል።
የ30 ዓመቱ ሴኔጋላዊ ኮከብ ሳዲዮ ማኔ በሊቨርፑል ቆይታው በ269 ጨዋታዎች 120 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ፣ ቻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ በርካታ ዋንጫዎች ማንሳት የቻለ የክለቡ ወሳኝ ተጨዋች መሆኑ ይታወቃል።
በሳዲዮ ማኔ ፊታውራሪነት የሚመራው የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን የግብጽ አቻውን በፍጻሜ ጨዋታ በመርታት ባሳለፍነው የካቲት ወር የአፍሪካ ዋንጫ ማንሳቱም አይዘነጋም።
“ላየንስ ኦቭ ቴራንጋ (የቴራንጋ አንበሶች)” በመባል የሚታወቀው የሰኔጋል ብሄራዊ ቡድን አሁን ላይ የቤኒን አቻውን ማሸነፉን ተከትሎ በምድቡ የሚገኙትን ማዳጋስካር እና ሩዋንዳን በማስከተል ምድቡን መምራት ጀምሯል።