ኢንተርኔት በመዝጋት ከፍተኛ ገቢ ያጡ 10 የአፍሪካ ሀገራት የትኖቹ ናቸው?
ከሰሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት በ2024 ኢንተርኔት በመዝጋት 1.56 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ ደርሶባቸዋል ነው የተባለው
ኢትዮጵያ ኢንተርኔትን በማቋረጥ ከአለም ስምንተኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ሪፖርት አመላከተ
ኢትዮጵያ ኢንተርኔትን በማቋረጥ ከአለም ስምንተኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ሪፖርት አመላከተ፡፡
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 አመት የኢንተርኔት መዘጋት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ሲገለጽ፤ በ 28 ሀገራት 167 የኢንተርኔት መዘጋቶች መመዝገባቸው ተነግሯል፡፡
በኢንተርኔት አጠቃቀም እና ደረጃ ላይ ሪፖርቶችን የሚያወጣው “ቶፕ ቴን ቪፒኤን” እንዳለው እነዚህ በመንግስት ተግባራዊ የሚደረጉ የኢንተርኔት መቆራረጦች 7.69 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራን በማድረስ በአለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ 648.4 ሚሊዮን ሰዎች በቀጥታ በነዚህ መስተጓጎሎች ከተለያዩ የኢንተርኔት አገልግሎቶች የተቋረጡ ናቸው ተብሏል፡፡
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ለ32,938 ሰዓታት የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት 1.56 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ኪሳራን ያስከተለ ሲሆን ይህም 111.2 ሚሊየን ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማድረሱ ነው የተዘገበው፡፡
የኢንተርኔት መዘጋት ከበይነመረብ ሳንሱር ዓይነቶች አንዱን ይወክላል ያለው ሪፖርቱ፤ የመረጃ ተደራሽነትን ፣ አስፈላጊ አገልግሎቶችን እና የዲጂታል መሠረተ ልማትን ማቋረጥ እንደሚያጠቃልል ያትታል፡፡
በ2024 የኢንተርኔት መዘጋት ያደረሰው ኪሳራ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ15.8 በመቶ የቀነሰ ቢሆንም ፤ ሆን ተብሎ የሚደረግ የኢንተርኔት መዘጋት ከበፊቱ በበለጠ ለብዙ ሰአታት መቆራረጡን የ”ቶፕ ቴን ቪፒኤን” ሪፖርት ጠቅሷል፡፡
እነዚህ መቆራረጦች 88,788 ሰአታትን የፈጁ ሲሆን ይህም ከ2023 ጋር ሲነፃፀር የ12 በመቶ ጭማሪ የታየበት ነው።
ከዚህ ውስጥ 49,101 ሰአት ሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ሲሆን፤ 39,687 ሰአታት የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ብቻ ኢላማ ደረጉ ነበሩ፡፡
አንድ ሶስተኛው የመንግስት የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ በ2024 ከተጨማሪ የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር የተቆራኘ ሲሆን ይህም ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ እና መረጃ የማግኝት ነፃነትን የሚገድብ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በአፍሪካ ኢንተርኔትን በማቋረጥ ቀዳሚዋ የሆነችው ሱዳን ስትሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በሶስተኛነት ተቀምጣለች፡፡
ሱዳን ለ12,707 ሰአታት ኢንተርኔትን በማቋረጥ 1.12 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ ስታስተናግድ 23.4 ሚሊየን ሰዎች ደግሞ አገልግሎት ተቋርጦባቸዋል፡፡
በሁለተኛነት የምትገኝው ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ በስምነተኛነት ስትቀመጥ የደረሰባት ኪሳራ ደግሞ 211.2 ሚሊየን ዶላር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ኬኒያ ፣ አልጄሪያ ፣ ጊኒ ፣ሞሪታንያ ፣ ሴኔጋል ፣ ሞዛምቢክ ፣ ቻድ እና ማውሪሽየስ በአፍሪካ ከ3-10 ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡