በጀቱ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን አህጉራዊ ጥረት ለመደገፍ የሚውል ነው
የአፍሪካ ልማት ባንክ ለድጎማ የሚውል 10 ቢሊዬን ዶላር መደበ
የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኮሮና ወረርሽኝ ምላሽ የሚሰጥ ቡድን ማቋቋሙን አስታውቋል፡፡
ቡድኑ አባል ሃገራቱ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት ይደግፋል ያለው ባንኩ በአህጉሪቱ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማቅለል የሚያስችል 10 ቢሊዬን ዶላር የድጎማ በጀት መመደቡንም ይፋ አድርጓል፡፡
በጀቱ አባል ሃገራቱ በወረርሽኙ ምክንያት ሊደርስባቸው ከሚችለው ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት ለማገገም የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ የሚውል ነው፡፡
የግልና የመንግስት አቅምን ለመደጎም እንደሚውልም የባንኩ ፕሬዝዳንት አኪንዉሚ አዴሲና ለባንኩ የቦርድ አመራር ገልጸዋል፡፡
የበጀቱ አጋማሽ (5 ነጥብ 5 ቢሊዬን ዶላር ያህሉ) ባንኩ በአባል ሃገራቱ በራሱ ለሚያስተዳድራቸው ተግባራት መደጎሚያነት፣3 ነጥብ 1 ቢሊዬን ዶላሩ በአፍሪካ የልማት ፈንድ በታቀፉ ሃገራት ለሚከናወኑ ተግባራት ማስፈጸሚያነት ቀሪው 1 ነጥብ 3 ቢሊዬን ዶላር ደግሞ የግል ተቋማትን ለመደገፍ የሚውል ነው እንደ ባንኩ መግለጫ፡፡
ባንኩ ከሁለት ሳምንታት በፊት ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚያስችል እና ሪከርድ የሰበረ የ3 ቢሊዬን ዶላር የማህበራዊ ቦንድ ሽያጭን በዓለም አቀፍ ገበያዎች አቅርቧል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንትም የባንኩ የቦርድ አመራር የዓለም የጤና ድርጅት በአህጉሪቱ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለማገዝ የሚያስችል የ2 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ አጽድቋል፡፡