“ሱዳን በአማጺያን እጅ አለመውደቋን እስከምናረጋግጥ ድረስ እንታገላለን” - አልቡርሃን
የሱዳን ጦር መሪው ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በካርቱም ወታደሮቻቸውን ጎብኝተዋል
የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች ትናንት የተጠናቀቀውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማራዘም ተስማምተዋል
የሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት ፕሬዝዳንት እና የሀገሪቱ ጦር መሪው ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በካርቱም የሚገኙ ወታደሮቻቸውን ጎብኝተዋል።
ጀነራል አልቡርሃን “የሱዳን ህዝብ ለሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፏል” ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
“ጦሩ ሙሉ የጦር መሳሪያውን አልተጠቀመም” ያሉት አልቡርሃን፥ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በድርጊቱ ከገፋበት ግን ጦሩ በሙሉ ትጥቁ መዋጋት ይጀምራል ሲሉም አሳስበዋል።
ጦሩ በሁሉም ክፍለጦሮች በሙሉ ሃይሉ ዝግጁ መሆኑንም ነው በጉብኝታቸው ወቅት ያነሱት።
የሱዳን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ በአደባባይ የታዩት ጀነራል አልቡርሃን፥ ጦሩ ድል እስኪቀናው ድረስ መዋጋቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
“ድል እስክንጎናጸፍና ሀገራችን በአማጺያን እጅ አለመውደቋን እስከምናረጋግጥ ድረስ እንታገላለን” ሲሉም ነው ወታደሮቻቸውን ያበረታቱት።
ይህ አስተያየታቸውም ሚያዚያ 15 2023 የተጀመረው ጦርነት በድርድር የመቋጨቱን ጉዳይ አሁንም አጠራጣሪ አድርጎታል።
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሹ ሃይል በአሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ አደራዳሪነት ለሰባት ቀናት ተኩስ ለማቆም የደረሱት ስምምነት በትናንትናው እለት ተጠናቋል።
ይህንኑ የተኩስ አቁም ለአምስት ቀናት ለማራዘምም መስማማታቸው ተገልጿል።
በካርቱም ጦሩ የሚገኝበትን ጣቢያ የጎበኙት አልቡርሃንም የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለንጹሃን መሰራታዊ አገልግሎቶችን ለማድረስ ያለመ ስለመሆኑ ጠቅሰው አማጺያን ሲሉ የገለጿቸውን የአርኤስፍ ሃይሎች ተጠያቂ አድርገዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ የንጹሃንን ንብረት ከመዝረፍ ተሻግሮ በማሰቃየትና በግድያ ላይ ተሰማርቷል ማለታቸውንም ሱዳን ኒውስ አስነብቧል።
አርኤስኤፍ በበኩሉ የሱዳን ጦር የተደረሱ የተኩስ ማቆም ስምምነቶችን በመጣስ የአየር ድብደባውን መቀጠሉን ገልጿል።
አለምአቀፉ ማህበረሰብ በሱዳን ግጭት የማቆም ስምምነት እንዲደረስ የሚያደርገው ጥረት እስካሁን ፍሬ አላፈራም።