የሱዳን ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም ተስማሙ
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ፍጹምነት የጎደለው ቢሆንም ወደ ሁለት ሚሊዮን ለሚገመቱ ሰዎች እርዳታ ለማድረስ በር ከፍቷል ተብሏል
ሳዑዲና አሜሪካ የተራዘመው ስምምነት ዘላቂ ግጭትን ለማስቆም መወያያ ጊዜ ይሰጣል ተብለዋል
የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ሰኞ ያለቀውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለአምስት ቀናት ለማራዘም ተስማምተዋል።
ስምምነቱ ከታደሰ በኋላ በዋና ከተማው ካርቱም ከባድ ግጭቶች እና የአየር ድብደባዎች መፈጸማቸው ሰብዓዊ ቀውሱን ለማቃለል የተደረሰው ስምምነት ውጤታማነት ላይ አዲስ ጥርጣሬ ፈጥሯል።
ለሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነትን ያደራደሩትና የሚከታተሉት ሳዑዲ አረቢያ እና አሜሪካ ስምምነቱ ከመጠናቀቁ ጥቂት ቀደም ብሎ ተፋላሚዎቹ እንዲራዘም መስማማታቸውን አስታውቀዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ፍጹምነት የጎደለው ቢሆንም፤ ወደ ሁለት ሚሊዮን ለሚገመቱ ሰዎች እርዳታ ለማድረስ መፍቀዱን ሁለቱ ሀገራት በጋራ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።
"ማራዘሚያው ለተጨማሪ ሰብአዊ እርዳታ፣ አስፈላጊ አገልግሎቶችን መልሶ ለማቋቋም እና ዘላቂ ግጭትን ለማስቆም ለመወያየት ጊዜ ይሰጣል" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ግጭቱ ከጀመረ በኋላ በካርቱም የመጀመሪያውን ምግብ ማከፋፈል መቻሉን ገልጿል።
የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በስልጣን ሽኩቻ ሚያዝያ 15 ወደ ግጭት መግባታቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ ወደ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።