ሄሜቲ በድምጽ መልዕክታቸው “የአልቡርሃን እጣፈንታ” ምን ይሆናል አሉ?
ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ በተቀረጸ የድምጽ መልዕክታቸው፥ ተገድለዋል በሚል የሚሰራጨውን ዜና አስተባብለዋል
የሱዳን ጀነራሎች የእርስ በርስ ክስና ዛቻ መቀጠሉ የተጀመሩ የሰላም ጥረቶችን እንዳያውኩ ስጋት ፈጥሯል
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) መሪው ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ በድምጽ ያስተላለፉት መልዕክት ተለቋል።
የጀነራል ዳጋሎ (ሄሚቲ) የድምጽ መልዕክት “ይድረስ ለመላው የሱዳን ህዝብ፣ ለፈጥኖ ድራሽ ሃይል እና ለሱዳን ጦር አባላት” በማለት ይጀምራል።
“እናንተ የሱዳን ምድርን እና ዜጎቿን ጠባቂዎች ናችሁ፤ ሱዳን በናንተ ነው የምትተማመነው፤ ከህዝቡ ጋር በቅርበት ተነጋገሩ፤ የህዝቡን ፍላጎት ተረዱ፤ ንጹሃንን የሚያሸብሩ አካላትንም ተፋላሟቸው፤ እኛ ማንኛውንም ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ነው” ሲሉም አስከተሉ።
ጀነራሉ ተገድለዋል በሚል ሲናፈስ ስለነበረው መረጃም ምላሽ ሰጥተዋል።
“እኔ በኦንምዱርማን፣ ባህሪ፣ ካርቱም፣ ምስራቅ ናይል እገኛለሁ፤ ጦሬን እየተንቀሳቀስኩ እመራለሁ፤ ነገር ግን ዳጋሎ ተገድሏል የሚሉ አሉባልታዎችን እያሰራጩ ነው፤ እኔ ግን በጥሩ ጤንነት ላይ እገኛለሁ” ሲሉም በተቀዳው ድምጽ ይደመጣሉ።
ስለጀነራል አልቡርሃን ሲናገሩም፥ “በቅርቡ በክንዳችን ስር ይወድቃል፤ ለእውነተኛ ፍትህም ይቀርባል” ብለዋል።
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ተደራዳሪዎች በቅርቡ በሳኡዲዋ ጂዳ በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ማሳወቃቸውን ይታወሳል።
ሁለተኛው ዙር ድርድርም በጂዳ እንደሚቀጥል በተነገረ ማግስት የተሰማው የጀነራል ዳጋሎ የድምጽ ቅጂ ግን ጦርነቱ በአጭር ጊዜ የመቋጨቱን ጉዳይ አሳሳቢ አድርጎታል።
ተፋላሚዎቹ ለ10 ቀናት ተኩስ ለማቆም በሳኡዲ እና አሜሪካ አደራዳሪነት ደርሰውታል የተባለው ስምምነትም ተጥሶ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጦርነቱ መቀጠሉ ተገልጿል።