የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዌንዲ ሸርማን ወደ ቻይና ሊያቀኑ ነው
ሸርማን ከቻይና ጉብኝታቸው በኋላ ወደ ጃፓን፣ደቡብ ኮሪያ እና ሞንጎሊያ ያቀናሉ ተብሏል
የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዌንዲ ሸርማን ታይጂን የተባለችውን የቻይና ግዛት ይጎበኛሉ ተብሏል
የዋሸንግተን እና የቤጅንግ እሰጥ አገባ በጋለበት በዚህ ወቅት የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቻይናን ሊጎበኙ ነው ተብሏል፡፡
ሚኒስትሯ ዌንዲ ሸርማን ወደ ቻይናዋ ታይጂን ጉብኝት እንደሚያደርጉ አሶሺትድ ፕሬስና ሲጂቲኤን ዘግበዋል፡፡ ሸርማን ዕሁድ እና ሰኞን በቻይና እንደሚቆዩ የተገለጸ ሲሆን ይህም ሁለቱ ሀገራት ከተነጋገሩና ከተደራደሩ በኋላ የመጣ የጉብኝት መርሃ ግብር መሆኑ ተገልጿል፡፡
ምክትል ሚኒስትሯ ቻይናን ሲጎበኙ ከሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ከመገናኘት ይልቅ ዝቅተኛ አመራርነት ላይ ያሉት እንዲያገኟቸው ታቅዶ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ይህንን የሰሙት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጉብኝቱ ምክትል ሚኒስትሯ ከከፍተኛ ባለስልጣኖች ጋር ካልተገናኙ ጉብኝቱ እንዲቀር አዘው እንደነበር ተገልጿል፡፡ የጉብኝቱ ሙሉ ዝርዝር እስካሁን ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ባይደረግም ሸርማን ግን ከከፍተኛ የቻይና ባለስልጣናት ጋር እንደሚገናኙ አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ምክትል ሚኒሰትሯ፤ በሰሜን ምስራቅ ቻይና በምትገኘው ታያንጅን ከተማ በሚኖራቸው ቆይታ ያገኟቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት የቻይና ባለስልጣናት መካከል ውጭ ጉዳይ ሚነስትር ዋንግ ይ አንዱ ናቸው ተብሏል፡፡
ምንም እንኳን የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና አሁን የጆ ባይደን የአየር ንብረት መልዕክተኛ የሆኑት ጆን ኬሪ ሚያዚያ ላይ ወደ ሻንጋይ አቅንተው የነበረ ቢሆንም ሸርማን በአሁኑ የአሜሪካ አስተዳደር ቻይናን የጎበኙ ትልቅ ባለስልጣን ይሆናሉ፡፡ ባለፈው መጋቢት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ከቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ጋር በአሜሪካ አላስካ መገናኘታቸው ይታወሳል፡፡
ሸርማን፤ ከቻይና ጉብኝታቸው በኋላ ወደ ጃፓን፣ደቡብ ኮሪያ እና ሞንጎሊያ እንደሚያቀኑ የተገለጸ ሲሆን ወደ ኦማን ለመሄድም ዕቅድ ይዘዋል ተብሏል፡፡