በተመድ ስብሰባ ሩሲያ፣ ቻይና እና ህንድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን ተቃወሙ- አምባሳደር ዲና
አምባሳደር ዲና የተቋረጠው የግድቡ ድርድር በቀጣይ ሳምንት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል
አምባሳደሩ የፀጥታው ምክር ቤት በትግራይ ክልል ስላለው ጉዳይ በቂ ግንዛቤ ስለሌለው ስብሰባ መቀመጡን ገልጸዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የጸጥታው ምክርቤት ስብሰባ ላይ “የኢትዮጵያ ወዳጅ” የሆኑት ሩሲያ፣ቻይናና ህንድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቀ መግባት እንደማያስፈልግ መናገራቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡
አምባሳደር ዲና ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ሌሎች የምክርቤቱ አባላትም የሶስቱን ሀገራት አቋም እንዲያራምዱ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይቻል ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት አምባሳደሮች እና ተወካዮች መልዕክት መተላለፉን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ዲና እንደገለፁት በቂ ግንዛቤ ካለመፈጠሩ የተነሳ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል ስላለው ጉዳይ ስብሰባ መቀመጣቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ያሰቡ ሀገራት ጉዳያቸው እንደማያስኬድና እውነታውን በቅጡ እንዲረዱት የሚያስችል ማብራርያ መሰጠቱንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
በማብራሪያው በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች እርዳታ እየደረሰ መሆኑንና ሰብአዊ እርዳታ ለሚያደርጉ ድርጅቶችም ክፍት መሆኑን መነሳቱ ተገልጿል፡፡አስር ሀገራት ተለዋጭ አባላት እንዲሁም አምስት ቋሚ አባላት ባሉበት የፀጥታው ምክር ቤት የየሀገራቱ ተወካዮች በተገኙበት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያላቸውን ጥያቄ እና አስተያያት እንዲሰነዝሩ ዕድል መሰጠቱን አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
ስለ ሱዳንና ግብጽ ስምምነት የተጠየቁት አምባሳደር ዲና፤ የሱዳን እና የግብጽ ስምምንት ኢትዮጵያ ላይ ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ ለሁለቱም አገራት የሚጠቅም እንደማይሆንም ማስጠንቀቅያ አዘል ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር በኩል ያለው ግጭት ምንም ለውጥ እንዳላሳየ፤ ሱዳን ቀድሞ ወደነበረችበት ስፍራ ስትመለስ ኢትዮጵያ ወደ ድርድር ለመመለስ ዝግጁ መሆኗንም ቃለ አቀባዩ ዳግም አረጋግጠዋል።
በህዳሴው ግድብ ጉዳይ በተመለከተ የአዲሷ አደራዳሪ አገር ኮንጎ ሪፐብሊክ ልኡካን በካርቱም፣ ካይሮ እና አዲስ አበባ ላይ የየሀገራቱን ስሜት ለመረዳት እና መረጃ ለማሰባበስ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆኑና በቀጣይ ሳምንታት የተቋረጠው የሦስትዮሽ የህዳሴ ግድብ ድርድር ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ቃለ አቀባዩ ተናግረዋል፡፡