መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት ተጠቅሞበታል ሲል አምነስቲ ከሰሰ
ዳይሬክተሯ የመንግሰት ባለስለጣናት በጅምላ ማሰራቸውንም ማቆም አለባቸው ብለዋል
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን "ታዋቂ ፖለቲከኞችን እና ጋዜጠኞችን" በማሰር ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ለማፈን ተጠቅሞታል ሲል ከሷል
መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት ተጠቅሞበታል ሲል ከሰሰ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን "ታዋቂ ፖለቲከኞችን እና ጋዜጠኞችን" በማሰር ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ለማፈን ተጠቅሞታል ሲል ከሷል።
በአማራ ክልል ባለፈው አመት ሀምሌ ወር የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜው ሲጠናቀቅ መንግስት "የሚቀሩ ሰራዎች" መኖራቸውን በመጥቀስ ጥር መጨረሻ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም አድርጎታል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ)፣ የአውሮፖ ህብረት እና አሜሪካ በሰብአዊ መብት ጉዳይ ችግር ይፈጥራል ሲሉ ስጋታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል አዋጁ ተግባራዊ በሆነባቸው ባለፉት ስድስት ወራት የመንግስት ባለስልጣናት ተጠርጣሪዎችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲይዙ፣ ሰአት እላፊ እንዲጥሉ፣ የመንቀሳቀስ መብት እንዲገድቡ እና ህዝባዊ ስብሰባ እንዲከለክሉ እንዳስቻላቸው ገልጿል።
በመግለጫው የድርጅቱ የምስራቅ እና የደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ቲገሬ ቻንጉታህ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰበብ በማድረግ መሰረታዊ መብቶችን መገደብ ማቆም አለበት ብለዋል።
ዳይሬክተሯ አክለውም እንደገለጹት "የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ገና በነጋሪት ጋዜጣ አልታተመም። ይህ የግልጽነት ችግር መረጃ የማግኘት እና የህጋዊነት መርህን የሚጥስ እንዲሁም ኢትዮጵያውን ህግ እየተከበረ ስለመሆኑ እንዳያውቁ ያደርጋቸዋል።"
ድርጅቱ በመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስድሰት ወራት ወቅት እና ከተራዘመ በኋላ መንግስትን የተቹ አምስት ፖለቲከኞች እና ሶስት ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ከቤተሰቦቻቸው ማረጋጠጡን ጠቅሷል።
ድርጅቱ እንደገለጸው የታሰሩት ፖለቲከኞች የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ዶክተር ካሳ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ዩሀንስ ባያለው፣ የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ታየ ደንደአ ሲሆኑ የታሰሩት ጋዜጠኞች ደግሞ አባይ ዘውዱ፣ በቃሉ አላምረው እና በላይ ማናየ ናቸው።
ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተራዘመ በኋላ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን በመተቸት የሚታወቁትን የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል የነበሩት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔን ማሰሩን ገልጿል።
ዳይሬክተሯ የመንግሰት ባለስለጣናት በጅምላ ማሰራቸውንም ማቆም አለባቸው ብለዋል።
ዳሬክተሯ መንግስት ታዊቂ ፖለቲከኞችን እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሁሉም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ ሰዎች ክስ እንዲመሰረትባቸው ወይም እንዲለቀቁ በማድረግ ሀገራዊ አለምአቀፋዊ ህጎችን ማክበር እንደሚገባው አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረቡበት ወቅት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መለቀቀቸውን እና በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ ታስረው እንደሚገኙ መግለጻቸው ይታወሳል።
በአማራ ክልል ያለው የትጥቅ ግጭት በንጹሃን ላይ የሞት እና የመቁሰል አደጋ እያደረሰ እንደሚገኝ ኢሰመኮን ጨምሮ አለምአቀፍ የመብት ተቋማት በተለያየ ጊዜ ሪፖርት አውጥተዋል።
የአሜሪካ መንግስት በክልሉ ያለው ግጭት በንግግር እንዲፈታ እንደሚፈለግ ገልጿል።