በአማራ ክልል ያሉ "ጽንፈኞች" መሳሪያ የሚያስቀምጡ ከሆነ መንግስት ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመንግስት ጋር የማይቀየር ዘላቂ የህገመንግስት ማሻሻያ እንዲደረግ ተናግረዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት ከሸኔ ጋር ያደረገውን ድርድር ግልጽ አላደረገም በሚል የተነሳባቸውን ትችት አጣጥለውታል
በአማራ ክልል ያሉ "ጽንፈኞች ኃይሎች" መሳሪያ የሚያስቀምጡ ከሆነ መንግስት ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገረ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ያሉት በዛሬው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርበው በሀገሪቱ የሰላም ጸጥታ ጉዳይ ማብራሪያ በሰጡት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ለታጣቂ ኃይሎቹ የሰላም ጥሪ ማድረጉን እና በጥሪው መሰረት ከጫካ የተመለሱ መኖራቸውን ገልጸዋል።
እስካሁን በአማራ እና በትግራይ ክልሎች በነበሩ ግጭቶች ኪሳራ መድረሱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ቢሆን የታጣቁ ኃይልች ትጥቅ ከፈቱ መንግስት ለንግግር ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በክልሉ፣ መንግስት ጽንፈኛ በሚላቸው የፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት የተቀሰቀሰው ባለፈው ሚያዚያ ወር ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ ከአማራ ክልሉ ግጭት ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ መንግስታቸው በክልሉ ህዝብ ለሚነሱ የልማት፣ የይገባኛል ጥያቄዎች እና የህገመንግስት ማሻሻያ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል።
ደርግ ወደ ስልጣን ሲመጣ የንጉሱን ህገ መንግስት መቅደዱ እና ኢህአዴግ የደርግን ህገ መንግስት መቅደዱ ትክክለኛ አካሄድ አለመሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመንግስት ጋር የማይቀየር ህገመንግስት እንዲኖር እንደሚደረግ እና በዚህም የአማራ ክልል ጥያቄ እንደሚመለስ ተናግረዋል።
በክልሉ ስለሚነሱት የይገባኛል ጥያቄዎች በተመለከቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝበ ውሳኔ ተደርጎ ህዝቡ ወደፈለገበት እንዲተዳደር ይደረጋል ብለዋል።
ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እና በውይይት ካልተፈታ ለአማራም ሆነ ለትግራይ የማይጠቅም እና ዘላቂ መፍትሄ የማያመጣ ነው ብለዋል።
መንግስት ካቀረበው የህዝበ ውሳኔ ውጭ ሌላ መፍትሄ ሁለቱ ወገኖች ተመካክረው የሚያመጡ ከሆነ መንግስት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የኦነግ ሸኔ ድርድር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት ከሸኔ ጋር ያደረገውን ድርድር ግልጽ አላደረገም በሚል የተነሳባቸውን ትችት አጣጥለውታል።
ኦነግ ከኤርትራ ወደ ሀገር ሲገባ ምን ቃል ተገብቶለት ነው?፤ ምን ስላልተፈጸመለት ነው ችግር የፈጠረው የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኦነግ እንደማንኛውም አማጺ በይፋ ጥሪ ተደርጎለት ነው የገባው ሲሉ ተናግረዋል።
ለግንቦት ሰባትም፣ ለኦብነግም እና ለኢሀፓም በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ የቀረበው በተወካዮች ምክርቤት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚቀርበውን ትችት አይቀበሉትም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኦነግን ብቻ የተለየ አድርጎ ማንሳት እና ነገሩን በሴራ ማየት ተገቢ አይደለም ብለዋል።
ከኦነግ ሽኔ ጋር በታንዛኒያ የተደረገው ድርድር ይህ ነው የሚባል ውጤት ስላላስገኘልን ለህዝብ ይህን አሳካን ማለት አልቻልንም ብለዋል።
ኦነግ ሸኔ "ወደፊት አደብ ገዝቶ ወደ ሰላም ከመጣ ለህዝብ እናሳውቃለን"።
ጠቅላይ ዐቢይ እክለውም ኦነግ በአስመራ በተደረገ ስምምነት ቃል የተገባለት ነገር ሳይፈጸምለት ቀርቶ ወይም ለህዝብ ተጨንቆ ከሆነ እታገልለታለሁ የሚለውን የኦሮሞ ህዝብ በመዝረፍ እና በማገት ተግባር አይሰማራም ነበር ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኦነግ ሸኔ ተግባር ለኦሮሞ ህዝብ ስለማይጠቅም ሀሳብ ይዞ ወደ ሰላም እንዲመጣ አሳስበዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት ጉዳይ
በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ግጭት የቋጨው የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በጋራ በመሆን ድሎች ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ባንኮች በ10ቢሊዮን ተንቀሳቃሽ ገንዘብ ስራ መጀመራቸው፣ በክልሉ ያሉ አየር መንገዶች ስራ መጀመራቸው፣ የ4ጂ የቴሌ ኔትወርክ አገልግሎት መጀመሩ፣ የኢንዱስትሪዎች ስራ መጀመር እና ሌሎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስኬት ያነሷቸው ተግባራት ናቸው።
ነገርግን ይህ በቂ አለመሆኑን እና የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
"እስር በዛ"
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እስር በዛ በሚል ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ እያታየ ካለው አናርኪ ወይም ህገወጥነት አንጻር በዝቷል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።
"መታሰር የሚገባቸው ሰዎች በየቀኑ እየታለፉ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እየታየ እንዳለው ሁኔታ ቢሆን ፖርክ ሳይሆን እስርቤት ነበር የምንገነባው ብለዋል።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የታሰሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መለቀቃቸውን እና አሁን የቀሩት በ100 የሚቆጠሩ ናቸው ብለዋል።
የቀሩትም ቢሆን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዙ እየያ እንደሚፈታቸው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት እንከን የለሽ እንዳልሆነ እና በመንግስት ውስጥ ያለ ወታደር፣ ፖሊስ ወይም ካድሬ ቁጥሩ ይነስ እንጁ ህዝብ የሚበድል አለ ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ይህን ችግር ለመፍታት የማጥራት ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።