በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የሚፈጸሙ ግድያዎች መቀጠላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
ግድያው በህክምና ላይ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ ሳይቀር ተፈጽሟል ብሏል ኮሚሽኑ
በ200 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል መፈጸሙንም ኢሰመኮ በሪፖርቱ አስታውቋል
በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የሚፈጸሙ ግድያዎች መቀጠላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል በቀጠለው ጦርነት ዙሪያ ያደረገውን የምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ባለው ጦርነት የደረሱ ጉዳቶችን ለመመርመር መንግሥታዊ ኃላፊዎችን፣ በግጭቱ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን፣ የዐይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችንና የተጎጂዎች ቤተሰቦችን በማነጋገር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ማሰባባቡን ነው ያስታወቀው።
ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በተለምዶ ፋኖ በመባል ከሚታወቀው አካል ጋር ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ይህ ጦርነት በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው ያለ ሲሆን በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን አመላክቷል።
በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በረኸት ወረዳ፣ መጥተህ ብላ ከተማ፣ በደብረ ማርቆስ ከተማ እንዲሁም በደንበጫ ከተማ በተፈጸመ የድሮን እና ከባድ መሳሪያ ጥቃት ሁለት ዓመት ያልሞላው ህጻንን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን መገደላቸውን ነው ሪፖርቱ የጠቆመው።
በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃትን በመሸሽ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ከቀያቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አረጋግጫለሁ የሚለው ኮሚሽኑ ከ3 ሺህ በላይ በምንጃር ወረዳ የአውራ ጎዳና ጎጥ ነዋሪዎች ከመስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደተፈናቀሉም አክሏል፡፡
በመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላት የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው ያለው ኢሰመኮ፥ የመንግሥት የጸጥታ አካላት በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪል ሰዎች ውስጥ “ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ፣ መሣሪያ አምጡ፣ የተኩስ ድምጽ ስለተሰማበት አቅጣጫ መረጃ ስጡ” በሚልና ይህንን በመሰሉ ምክንያቶች ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች እየተፈጸሙ ናቸውም ብሏል፡፡
ለአብነትም በባሕር ዳር ከተማ፣ ሰባታሚት አካባቢ መስከረም 29 እና 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ሦስት ወንድማማቾችን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች፣ በሰሜን ጎጃም ዞን፣ አዴት ከተማ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ፍልሰታ ደብረ ማሪያም የሚኖሩ 12 የአብነት ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ሲቪል ሰዎች፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ አማኑኤል ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢያንስ 8 ሲቪል ሰዎች በቤት ለቤት ፍተሻ ተገድለዋል ብሏል የኢሰመኮ ሪፖርት።
ከዚህ በተጨማሪም በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ፣ ግንደወይን ከተማ ሞጣ በር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም. አንድ በጥይት የቆሰለን ግለሰብ እናቱና እህቱ በባጃጅ አሳፍረው ወደ ሕክምና ተቋም በመውሰድ ላይ እያሉ፣ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ባጃጁን አስቁመው ሁሉንም ተሳፋሪዎች ካስወረዱ በኋላ “የቆሰለው እኛን ሲዋጋ ነው” በሚል ምክንያት የባጃጅ አሽከርካሪውን ጨምሮ አራቱን ሰዎች በጥይት እንደገደሏቸው ኮሚሽኑ ከነዋሪዎች ተረድቻለሁም ብሏል፡፡
በባሕር ዳር፣ በፍኖተሰላም፣ በጎንደር እና በወልድያ ከተሞች በትጥቅ ግጭቱ ቆስለው ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ የተወሰኑ ሲቪል ሰዎችና የታጣቂ ቡድኑ አባላት በመሆን በመንግሥት የጸጥታ አካላት የተጠረጠሩ ሰዎች ሕክምናቸው እንዲቋረጥ ተደርጎ ወዳልታወቀ ስፍራ ከተወሰዱ በኋላ፣ ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ወደ ሕክምና ተቋማቱ ሲመለሱ ቀሪዎቹ ያሉበት ሁኔታ ይህ መግለጫ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ ማረጋገጥ እንዳልተቻለም ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለ በየደረጃው የሚገኙ ሲቪል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ ግድያዎችና እገታዎች በታጠቁ ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባለ ሲሆን መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከባሕር ዳር ወደ ደብረ ታቦር ሲሄዱ አለምበር ከተማ አካባቢ በታጣቂዎች ተገድለዋል ተብሏል።
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች እንዲያመልጡ ተደርጓል የሚለው ኢሰመኮ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎም አሳሳቢ እንደሆኑም አስታውቋል፡፡
የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት በተለያዩ የጤና ተቋማት መድረስ የቻሉትን ተጎጂዎች ቁጥር ብቻ መሠረት በማድረግ፣ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ መግለጫ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ 200 የአስገድዶ መድፈር ተጎጂዎች በጤና ተቋማት መመዝገባቸውም ነው የተጠቀሰው።
የአስገድዶ መደፈር ወንጀሉ ከተፈጸመባቸው አካላት መካከልም የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሴቶች እና የጤና ባለሞያ ሴቶች ጭምር ይገኙበታል ተብሏል።
በክልሉ ያሉ በርካታ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ለወታደራዊ አገልግሎቶች እየዋሉ ነው ያለው ኮሚሽኑ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና ሌሎች የግለሰቦች ንብረቶች ለውድመት እና ዘረፋ መዳረጋቸውንም ኢሰመኮ ገልጿል፡፡
በክልሉ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትኩረት እንዲሰጥም ኢሰመኮ በሪፖርቱ አሳስቧል፡፡