ሳዑዲ በጎልፍ ውድድሩ ምክንያት የሚጎበኟትን ታላላቅ ሰዎች ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች
በፈረንጆቹ ከየካቲት አንድ እስከ ሰባት 2021 ድረስ ዓለም አቀፍ የጎልፍ ውድድር በሳዑዲ አረቢያ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡
በዚህ የጎልፍ ውድድር ላይ በርካታ የስፖርት ሰዎች፣ታዋቂ ግለሰቦች እና ኢንቨስተሮች እንደሚገኙና ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ውድድሩን የሳዑዲው ንጉስ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን በበላይነት ያዘጋጁታል፡፡
የሳዑዲ ጎልፍ ፌዴሬሽን እና የስፖርት ሚኒስቴር የጉብኝት ቪዛዎች በኤሌክትሮኒክ መንገድ (ኢ-ቪዛ) ለተሳታፊዎች እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ ለስፖርት ምርምር ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ የተገለጸው የልዑል ፈይሰል ቢን ፋሃድ ሽልማትም በዚሁ ጊዜ ይፋ እንደሚደረግ ነው የሚጠበቀው፡፡ ሽልማቱ በሳዑዲ አረቢያ የስፖርት ምርምር ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የሚደረግ ነው፡፡
ሽልማቱ ምርምርን ለመደገፍ እና ለጥያቄዎች መልስ በመስጠት ፣ በሳዑዲ አረቢያ ስፖርት ላይ አወንታዊ ለውጥ ለማምጣት መዘጋጀቱንም ነው ሀገሪቱ የገለጸችው፡፡
ለእያንዳንዱ የምርምር ፕሮጄክት ከ 80 ሺ እስከ 120 ሺ ዶላር የሚያወጡ ድጎማዎች የሚሰጡ ሲሆን አጠቃላይ የሽልማት ድጋፉ 1 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሏል፡፡ ሽልማቱ ሳዑዲ አረቢያ በአውሮፓውያኑ 2030 እደርስበታለሁ ያለችው ራዕይ አካል እንደሆነም ተገልጿል፡፡